በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡

መቅደስ ትሠራልኛለህ፡ በመካከላችሁም አድራለሁ፡፡ዘፀአ. ፳፭፥፰

እግዚአብሔር አምላክ ቦታ የማይወስነው በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚገኝ ቢሆንም በብሉይ ኪዳን ለነብዩ ለሙሴ መቅደስ እንዲሠራለት በማዘዝ በህዝበ እስራኤል መካከል በረድኤት የሚያድር መሆኑን ገልጿል፡፡ ስለ ቤተ መቅደሱም አሠራርና ይዘት ለሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በፆምና በጸሎት አሳይቶታል፡፡ ቤተ መቅደሱንም በተራራው ላይ ባሳየው ምሳሌ መሠረት እንዲሠራው አስጠንቅቆታል፡፡ ዘፀአ. ፳፭፥፱

1. ቤተ መቅደስ በብሉይ ኪዳን

ደብተራ ኦሪትን እንዲተክል እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ጊዜ ጀምሮ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በእስራኤላውያን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ትልቁንና ዋናውን ቤተ መቅደስ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም እጅግ በተዋበ አሠራር አርባ ዓመት በመገንባት ያሠራ ሲሆን እስራኤላውያን ሌሎች አነስተኛ ቤተ መቅደሶችን ምኩራብ በሚል ስያሜ በየመንደሩ ይሠሩ ነበር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ወደ ናዝሬት ገሊላ ተልኮ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ያበሰራት በናዝሬት በሚገኘው ቤተ መቅደስ ነበር፡፡ ሉቃ. ፩ ፥ ፳፩

2. የቤተ መቅደስ ክብርና ጸጋ

የቤተ መቅደስ ክብርና ጸጋ ትልቅና ከእያንዳንዱ ሰው መኖሪያ ቤት እንደሚበልጥ እግዚአብሔር ለነብያቱ እንዲህ በማለት ገልጿል፡፡ ይህንን ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው፤ ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር፡፡ ሐጌ. ፪ ፥ ፯

3. ቤተ መቅደስን ማገልገል ምን ጥቅም አለው?

እግዚአበሔርን ማገልገል ብዙ በረከት፣ ጸጋና ሠላም የሚያሠጥ መሆኑን በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት የምናነበው ሲሆን በተለይም ቤተ መቅደሱን ከፍ ለማድረግ ለሚሠራ ሰው የሚሠጠውን ሠላም እንዲህ በማለት ገልፆታል፡፡ይህን ቤተ መቅደስ ከፍ ለማድረግ ለምትሠራ ሰውነት ሁሉ ሰላምን እሰጣለሁ፡፡ ሐጌ. ፪ ፥ ፰

4. ቤተ መቅደስ በማን ስም ይጠራል?

እግዚአብሔር አምላክ ቤተ መቅደሱ የወዳጆቹ የቅዱሳን ሥም መታሰቢያ እንዲሆን ስለፈቀደ ቅዱሳት መካናት ሲታነፁ በቅዱሳን ሥም ይጠራሉ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ በማለት በነብያቱ አፍ ተናግሮአል፡፡  ሰንበታቴን የሚጠብቁትንና የማያረክሱትን፥ በቃል ኪዳኔም ጸንተው የሚኖሩትን ሁሉ፥ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአህዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና፡፡ ኢሳ. ፶፮፥ ፯

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ፡፡ ኢሳ. ፶፮፥ ፭

5. ምን እናድርግ?

ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ሚክ. ፫ ፥ ፯

አስቀድሞ ለሙሴ በኋላም ለነብያትና ለቅዱሳን ሁሉ እንደተነገረው አባቶቻችንም ህጉንና ትዕዛዙን ጠብቀው እንደተጓዙት ሁሉ በአከባቢያችንና በመኖሪያችን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ (ቤተ ክርስቲያን) መትከል፣ ከፍ ከፍ ማድረግና ማገልገል ይገባናል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን የሚድስና የሚያገለግል ቢመስለውም ቅድስናውና አገልግሎቱ ለራሱ ነው፡፡ በመሆኑም አጥቢያ አብያተ ከርስቲያናትን በመመሥረት፡ –

ሀ. እግዚአብሔር በረድኤትና በጸጋ በመካከላችን እንዲኖር እናደርጋለን፤

ለ. በሰንበትና በቅዱሳት በዓላት ቅዳሴውን እናስቀድሳለን ምሥጢራትን እንሳተፋለን፤

ሐ. ልጆቻችን ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንዲማሩ እናደርጋለን፤

መ. የክርስትናን ሕይወት በቃልና በኑሮ ለሌላው ሕዝብ እናስተምራለን፤

ሠ. ከቅዱሳን በረከት፣ ረድኤትና አማላጅነት እናገኛለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡ ማቴ. ፲፩ ፥ ፲፩ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ነብያት ነብይ፣ እንደ ሐዋርያት የወንጌል ሰባኪ፣ ካህን፣ ባህታዊ፣ ሰማዕትና ጻዲቅ ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ስም የተመሠረተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራክቪል፣ በጌትስበርግ፣ በፖቶማክና በጀርመን ታውን አካባቢ ተጀምሮአልና ከበረከቱ እንድንሳተፍ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

አብያተ ክርስቲያን