እንኳን ለ፳፻፲፬ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“እንደተናገረ ተነሥቷል” (ማቴ.28÷6)

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፣   ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ፣
በዐብይ ኃይል ወሥልጣን፣      በታላቅ ኃይልና ሥልጣን፣
ዐሠሮ ለሰይጣን ፣                ሰይጣንን አሠረው፣
አግዓዞ ለአዳም፣                  አዳምን ነጻ አወጣው፣
ሰላም                               ሰላም
እምይእዜሰ                        ከዛሬ ጀምሮ
ኮነ ፍስሐ ወሰላም፣              ደስታና ሰላም ሆነ!!!

የተወደዳችሁ የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያን አባላት በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ።
ሞት የሕይወት ፍጻሜ አለመሆኑን ከክርስቶስ ትንሣኤ እንማራለን። በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ የሥጋ ሞት ተስፋ የማያስቆርጥ ትንሣኤ ሕይወት እንዳለው ያመለክታል። ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኵር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን ነው። ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ትንሣኤ ስለ ዓለም ፍጻሜ የምታስተምረውን ትምህርት የማያውቁ ወይም የማይቀበሉ አንዳንድ ሰዎች ሕይወታቸው ሁሉ በሞት የሚያልቅ ይመስላቸዋል። እነዚህ ሰዎች የመንፈስ ጭንቀት የሚያሰቃያቸው ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ናቸው። ክርስቲያኖች ግን የራሳቸውን ትንሣኤ በክርስቶስ ትንሣኤ ያረጋገጡና የተማሩ ስለሆኑ ምድራዊ ሕይወታቸው ቢያልፍ ሰማያዊ ሕይወታቸው እንደሚጠብቃቸው ያምናሉ። 2ኛ ቆሮ 1፣4
የዘንድሮውን የ2014ዓም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ልዑል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያ ሁሉ አስጨናቂ እና የመከራ ወቅት አሳልፎ በሕይወት ስለጠበቀን እያመሰገነው ከመቃብር ባልተሻለ ኑሮ የሚኖሩትን በኃጢያት ዓለም የታሰሩትን፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚማቅቁትን ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን ልናስታውሳቸው ይገባል፣ በአገር ቤት በመከራ ውስጥ ሆነው የሚላስ የሚቀመስ ላጡት ልንረዳቸው ይገባል።
ውድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ክርስቶስ የተነሣው ለእኛ የትንሣኤ አብነት ሊሆነን ነውና “ክርስቶስ ተነሥቷል በመቃብሩ ውስጥ የለም ” እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ።
አሜን

 

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ
የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ

ሚያዝያ 16/2014 ዓ/ም