እንኳን ለዘመነ ማርቆስ ፳፻፲፬ በሰላም አደረሳችሁ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

የተከበራችሁ የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያን አባላት በቅድሚያ ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ /2013ዓም/ ወደ ዘመነ ማርቆስ /21014 ዓም/ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡
“ሕይወትን የሚወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚሻ፣ አንደበቱን ከክፉ፣ከንፈሮቹንም ተንኮልን ከመናገር ይከልከል፣ከክፉ ይራቅ፣መልካምንም ያድርግ ሰላምንም ይሻት፣ይከተላትም።”
1ኛ ጴጥ 3፣10-12
ያሳለፍነው ዘመነ ማቴዎስ ብዙ ተግባራት ያከናወንበት፤ ትሩፋትና በረከትም ውጤትም ያገኘንበት ዘመን ነበር፣ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ከወዳጁ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ታቦት ሕጉ ከብሮ በረከት ያገኘንበት ዘመን ነበር። የተወደዳችሁ ምእመናን ወንድሞች እህቶች የ2013ዓም የነበሩትን ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች አልፈን ለአዲሱ አመት ዘመነ ማርቆስ 2014ዓም እንድንደርስ ያበቃንን ልዑል እግዚአብሔር ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ እስከዚች ዕለትና እስከዚች ሰዓት አድርሶናልና፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው መልካሙን ቀን ለማየት የሚሻ አንደበቱን ክፉ ከመናገር የራቀ ሊሆን ይገባል፤ ዘውትር በማህበራዊ ሚዲያ ክፉ ሰምቶ፣ ክፉ በመናገር ክፉ ከመስራት ልንቆጠብ ይገባል። ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ንስሐችንን በመቀበሉ ስለተመረጡት ጥቂት ወዳጆቹ ብሎ ከዚህ አድርሶናል። በዘመነ ማርቆስ ዳግመኛም ከበደላችንና ከክፉ ሥራዎቻችን ወደ ንስሐ እስከምንመለስ በእኛ ላይ ይታገስ ዘንድ ከእኛ አስቀድሞ ብዙዎች አሕዛብን እንዳጠፋቸው ስለክፉ ሥራችን እንዳያጠፋን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡ እንግዲህ ክፋትን ከማሰብ ከመፈጸም ተከልክለን ከወደቅንበት እንነሳ፤ መልካምን እናድርግ ክርስትናችን በምግባር እናስመስክር ሰላምን መፈለግ ወይም በመሻት ወይም በመናገር ብቻ ልናመጣት አንችልም ሰላምን እስከመጨረሻው ሰላማዊ ሰዎች ሆነን ስንሰራት የሰላም ባለቤት የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰጠን በእምነት፣ በጽናት እና በትዕግስት ሕጉንና ትዕዛዙን ስንፈጽም ብቻ የምናገኘው በመሆኑ ነው። ይልቁንም በሀገራችን በኢትዮጵያና በሕዝቦቹዋ ላይ በተግባር የምናየው የጥፋት ማዕበል ፣ ወጀብ እና ነፋስ ሰጥ ማለት የሚችለው ሁላችንም ከበደላችን ንስሐ ገብተን ሰላምን ለምፍጠር ማንኛውንም ሰማዕትነት በመክፈል በአንድነት ስንቆም ነው። ስለአለፈው በደላችንና ስለብዙ ኃጢአታችን በፊቱ ልናለቅስ ወደርሱም ልንጮህ ይገባናል፡፡ በሕይታችን ዘመን ሁሉ ከጠላታችን ሰይጣን ወጥመድ ጠብቆ በነፍስ በሥጋም ጤነኞች እንደሆን በቀናች ሃይማኖትና በበጎ ሥራ ሁሉ ጸንተን ደስ እንዳለን እንደዛሬው ለመጪው ዐመት ያደርሰን ዘንድ እንለምነው፡፡ ከእኛም በተለያየ ምክንያት በሞት የተለዩትን በበጎ ዕረፍት እንዲያሳርፍልን፤ ሕጽናትና ወጣቶችን በጥበብና በሞገስ እንዲያሳድግልን ፤ በሀገራችን ጽጋብን በረከትን ይሰጥ ዘንድ የተራቡም እንዲጠግቡ የምድራችንን ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ በሽተኞቻችን ይፈወሱ ዘንድ፣ ሽማግሌዎቻችንና አሮጊቶቻችን የሙት ልጆችም ይጠበቁ ዘንድ ገበሬው አርሶ ያመርት ዘንድ ፤ ነጋዴውም ነግዶ ያተርፍ ዘንድ ለሀገራችንና ለዐለሙ ሁሉ ሰላም ይሁን አሜን፡፡
በመጨረሻም መጪው ዘመነ ማርቆስ /2013ዓም/ የበለጠ በመንፈሳዊ አገልግሎት ፍሬ የምናፈራበት፣ የሰላም የጤና የበረከት ዘመን እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ፡፡
እንኳዋን ለአዲሱ ዓመት ዘመነ ማርቆስ 2014 ዓም አደረሳችሁ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

 

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ
የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ

ጳጉሜን 5/2013 ዓ/ም