ልደታ ለማርያም

እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን አሜን።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰው ወገን ሁሉ የድኅነት ምክንያት ናት፡፡ ፍጥረታት ሁሉ እርሷን ያመሰግኗታል፡፡ የፍጥረት ሁሉ መዳን በእርሷ እጅ ነበርና፡፡ አዳም አባታችን በተሰደደ ጊዜ መጽናኛው እርሷ ነበረች፡፡ አዳም አባታችን ሲሰደድ አምላካችን በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑ ሲቃረብ ከእርሷ ሊወለድ እሷ ተወለደች፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ የእመቤታችን መወለድ አስቀድሞ በነቢያት የተነገረ፤ በብዙ ሕብረ አምሳል የተገለጠ ነው፡፡ በነገረ ማርያም እንደምንረዳው እመቤታችን ከመወለዷ አስቀድሞ ቅድመ አያቶቿ፣ አያቶቿና ወላጆቿ ምልክት አይተዋል፡፡

የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነዉ፡፡ ሊባኖስ ከገሊላ በስተሰሜንና ከፍንቄ በስተ ምስራቅ ይገኛል ፡፡ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ የሚለው ቃለ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ መኃ 4-7 ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታ መንገድ ጠራጊ፣ የአዋጅ ነጋሪና ታማኝ ምስክር በመሆኑ በተወለደ ጊዜ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ብሏል፡፡

ሉቃ 1-14 የቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ለብዙዎች ደስታና የምስራች አብሳሪ ከሆነ ድኅነተ ሥጋ ወነፍስ የሚሰጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ ያስደስት፡፡ የቀርጤሱ ቅዱስ እንድርያስ ስለ እመቤታችን ልደት እንዲህ ብሏል ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌዉ በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነዉ፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነዉ ብሏል፡፡

እመቤታችን ለፀሐዩ መምጣት የተዘረጋች ሰማይ፡ በቅድመ አያቶቿ በነቴክታና ጴጥሪቃ ሕልም እንደታየችዉ በሌሊት የምታበራ ጨረቃ፤ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ፤ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰዉ ልጅ ሁሉ ደስታ ነዉ፡፡ ነቢያት በብዙ ሕብረ አምሳል የተናገሩላት መሰረቶቿ የተቀደሱ ተራራዎች ናቸዉ፤ ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች አበባዋም ከግንዱ ይወጣል፤ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነይ ብለዉ ተናገሩላት፤ ልደቷ የትንቢታቸዉ ፍፃሜ ነዉና ደስታቸዉ ታላቅ ነዉ፡፡

መዝ 86፡1 ኢሳ. 11፤1 በእግዚአብሔር የሚያምኑ ጴጥሪቃና ቴክታ የሚባሉ በሀብት የከበሩና ደጋግ ባልና ሚስቶች በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ደጋግ ሰዎች በሀብት ይክበሩ እንጂ ሀብታቸውን የሚወርስ ልጅ አልነበራቸውም፤ መካን ነበሩ ። ከዕለታት አንድ ቀን ጴጥሪቃ ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ ሀብቱን ሰፍሮና ቆጥሮ ቴክታን እህቴ ሆይ ይህ የሰበሰብነው ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን? የሃብታችን ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ የሚወርሰን ልጅ የለን፡፡ አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት፡፡ እርሷም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተ ያለ ልጅ ትቀራለህን? ከሌላ ሴት ውለድ አለችው፡፡ ጴጥሪቃም እንዲህ ያለ ነገር እንኳንስ ላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት፡፡ እሷም እንግዲህ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ያውቃል፡፡

ትላንትና ማታ በሕልሜ ነጭ አንስት ጥጃ ከማኅጸኔ ስትወጣ፣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ ሰባት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ፤ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ አለችው:: እርሱም በጠዋት ከሕልም ፈቺ ዘንድ ሄዶ ቴክታ የነገረችውን ሕልም ለፈቺው ነገረው፡፡ ያም ሕልም ፈቺ እግዚአብሔር በምኅረቱ አይቷችኋል ሰባት አንስት ጥጆች መውለዳችሁ ሰባት ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፡፡ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው:፡

ጴጥሪቃም ሕልም ፈቺው የነገረውን ሁሉ ለቴክታ ነገራት፡፡ እርሷም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል? ብላ ዝም አለች፡፡ በዚያም ወራት ቴክታ ጸነሰች፡፡ በዘጠኝ ወሯ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ስሟንም ሄዔሜን ብለው አወጡላት፡፡ ሄዔሜን አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኗ ደርዲ ብለው ስም አወጡላት፡፡ ደርዲ ማለት ከአባቶች ወገን የተወለደች ማለት ነው:: ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደችና ቶና አለቻት፡፡ ቶና ማለት ራዕይ አይተን ነገር አግኝተን የወለድናት ማለት ነው):: ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት፡፡ ሲካር ማለት ከዘመዶቻችን የተወለደች ማለት ነው:: ሲካርም እንዲሁ አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ ባል አጋቧት ሴት ልጅም ወልደች፡፡ በስምንተኛ ቀን ስሟን ሴትና ብለው አወጡላት ፡፡ ሴትና ማለት ሙያዋ ያማረ፣ ምግባሯ የሰመረ በጎ ቆንጆ ማለት ነው፡፡ ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት፡፡ ሄርሜላ ማለት ከክቡሮች ከባለጸጋ ወገን የተወለደች ማለት ነው፡፡ ሄርሜላም እንዲሁ አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኗም ሐና ብለው ስም አወጡላት፡፡ ሐና ማለት ምን ማለት በሐይማኖት በምግባር የጸናች፣ በንጽሕና በቅድስና የተሸለመች ክብርት ወልዕልዕት ደግ ፍጥረት ማለት ነው፡፡

ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ ስድሳ ሰባት ወንዶች ልጆች አሉ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢት አልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆጠረላቸውምና አልተፃፈም፡፡ ሐና አደገች ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግሥት ወገን፣ ከዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት:: ቅዱሳን ኢያቄም እና ሐና ሲኖሩ ልጅ አጡ፡፡

ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኀዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሒደው ሲፀልዩ ሲያዝኑ ዋሉ፡፡ ኀዘናቸው እንዴትስ ነው? ቢሉ፡፡ ኢያቄም አቤቱ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔን ባርያህን ስማኝ፡፡ ጸሎቴን ተቀበል ለዐይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ልጅ ስጠኝ ብሎ ሲለምን ዋለ:: ሐናም በበኩሏ አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ ባርያህ እለምንሃለው፡፡ ለዐይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ልጅ የማኅፀኔን ፍሬ ስጠኝ ብላ ስትለምን ዋለች:: እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዋሉ፡፡

በዚህ ወቅት ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ አምርራ አለቀሰች፡፡ ወዲያው ከሊቀ ካህናቱ ከዘካርያስ ዘንድ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፡፡ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ተሳሉ ። ሊቀ ካህኑ ዘካርያስም እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላችሁ ብሎ ጸሎታቸውን አሳረገላቸው፡፡

ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ሀሳባቸውን ተመለከተ፡፡ ኢያቄምና ሐና በዕለቱ ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩም ኢያቄም ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ ለሐና ነገራት ሐናም እኔም አየሁ አለችው፡፡ ምን አየሽ ቢላት? ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው:: ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ነጭነቷ ንጽህናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቷ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሷ ነው፤ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ነው።

እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉዓት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን መልአኩ ከሰው የላቀች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሷን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ አላቸው፡፡

በፈቃደ እግዚአብሔር በብስራተ መልአክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች፡፡ እመቤታችን በተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው፡፡ ቅናቱ እንዴት ነው? ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ከአጎቱ ቤት ሔዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው በአልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡ የሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆይዋት:፡፡ እርሷ አብራ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል የሞተው ልጅ ብድግ ብሎ ተነሳ፡፡

ሕዝቡ ሁሉ ተገረሙ ተደሰቱ አይሁድ አብረው ነበሩና ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከሐና ማኅፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን እመቀ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች፡፡ እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ፡፡ እኔንም ያስነሳችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት አላቸው፡፡ ያን ጊዜ አይሁድ እነዳዊት እነሶሎሞን አባቶቻችንን 40፣ 40 ዓመት እንደ ሰም አቅልጠው፤ እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙ፡፡ ከሐና የሚወለደውም እንዲሁ ሊገዛን ነውን? ብለው ሳይወለድ እንግደለው ብለው ሊገድሉ ያስቡ ነበር፡፡

መልአኩም አይሁድ እንዳያገኟቸው ወደ ሊባኖስ እንዲሰደዱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በሊባኖስ ግንቦት 1 ተወለደች:: እመቤታችን በተወለደችበት ዕለት ደስታ ተደረገ፡፡ ቤታቸው በብርሃን ተመላው በስምንተኛውም ቀን ማርያም ብለው ስም አወጡላት:: በዚህ መሰረት የእመቤታችንን የልደት በዓል(ግንቦት ልደታ) በታላቅ ክብር ከሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት መካካል ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት፡፡

የግንቦት ልደታ በዓል አከባበር በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት መሰረት ኢያቄምና ሐና ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ ምግባቸው ንፍሮና ጥራጥሬ ስለነበር ይህንን ትውፊት መሰረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን በማኅሌት፣ በቅዳሴና ታቦታትን በማክበር፣ ከመኖሪያ ቤት ዉጭም ቂጣ ተጋግሮ፤ ንፍሮ ተቀቅሎ እየተበላ ይከበራል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሯ አማላጅነቷ በሁላችን ይደር፡፡ አሜን፡፡

መ/ር ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ

ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም

ምንጭ https://m.facebook.com/shegetube/posts/1407247329389670