በዓለ ልደት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ፤ ምሥጋና ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፡፡ሉቃ ፪፥፲፬

ይህን መዝሙር የዘመሩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ የዘመሩትም መሲህ ክርስቶስ የሰማይና የምድር ንጉስ፣ በቤተልሔም መወለዱን ለእረኞች ባበሠሩበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከእረኞች ጋር አብረው ዘምረዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ ቀድሞ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ተገንብቶ የነበረውን የጥል ግድግዳ እንዲፈርስ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በፈጣሪና በፍጡራን፣በሰማውያንና በምድራውያን መካከል፤ አምላክና በሰው መካከል ዕርቅ ሆነ፤ ሰላም ሆነ፡፡ ስለዚህም ምድራውያን እረኞች እና ሰማያውያን መላዕክት በደስታ በአንድነት ዘመሩ፡፡

በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰባቱ መስተጻርራን /ተቃራኒ ነገሮች አንድ ሆነዋል፡፡ እነዚህም በጠብና በጦርነት ይፈላለጉ የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ ታርቀዋል፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ሰብዓ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ሥጦታ ይዘው ”አይቴ ሀሎ ንጉሠ አይሁድ ዘተወልደ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው“ ማቴ.2፥4 እያሉ መጥተው ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ገብረውለታል፡፡ ነፍስና ሥጋ፡- በሲዖልና በመቃብር ተለያይተው የነበሩ ነፍስና ሥጋ ከእመቤታችን ከነፍሷ ነፍስ ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው በሆነ ጊዜ ነፍስና ሥጋን አስታርቋል፡፡ ሰውና እግዚአብሔር፡- አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በልቶ የሰውና የእግዚአብሔር የልጅነት ግንኙነት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተቋርጦ ነበርና ጌታችን በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በተወለደ ጊዜ እርቀ ሰላም ሆኗል፡፡ ሰውና መላእክት፡- አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ጋር በተጣላ ጊዜ ቅዱሳን መላእክትም ስለተጣሉት በምትገለባበጥ ሰይፈ እሳት አስፈራርተው ከገነት ከአስወጡት በኋላ ወደ ገነትም እንዳይገባ ገነትን ይጠብቁ ነበር፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ አንድ ሆነው ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

ውድ የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተክርስቲያን ልጆች ባሳለፍነው አምስት ወራት ልዑል እግዚአብሔር በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አማላጅነት በአገልጋይ ካህናትና በምእመናን ሁለገብ ጥረትና ትጉህ ተሳትፎ ውጤታማ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ በረከትም አግኝተናል፤ ሁላችሁንም ልዑል እግዚአብሔር በረከቱንና የማያልፍ ርስቱን እንዲያወርሳችሁ ጸሎቴ ነው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች አጥቢያ በተክርስቲያናችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በሰላም በደስታ፤ በዝማሬ ለማክበር በዝግጅት ላይ እንገኞለን፡፡ይህ ቀን የተጣላን ካለን የምንታረቅበት ዕለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሰጠን ሀብት ለነዳያን፣ ላጡ፣ ለተቸገሩ በማካፈል በረከት የምናገኝበት ቀን ነው፡፡እግዚአብሔር የሰጠንን ጉልበት፣ እውቀት፣ ገንዘብና ሕይወት መልሰን ሥጦታ ለሱ የምናበረከትበት ዕለት ነው፡፡

በዓሉ ታኅሳስ 29 ቀን 2010 ዓም/Jan. 07/2018 ሲሆን በዓሉን ማክበር የምንጀምረው ቅዳሜ ታህሳስ 28 ቀን 2010 ዓም /Jan. 06, 2018/ ከምሽቱ 8:00pm ጀምሮ ስብሐተ እግዚአብሔር በማድረስ ይሆናል፡፡ በዚህ ዕለትም እኛም እንደመላዕክት የቤተክርስቲያናችን መልዕክተኞች ሆነን ወደ ቤተክርስቲያን ያልመጡትን ሁሉ በመጋበዝ የጌታን የልደት በዓል በቅዳሴ፣ በምስጋና እና በዝማሬ በድምቀት በአንድነት በደመቀ ሁኔታ ለማክበር እንድንችል በሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተክርስቲያን እንድንገኝ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

 
 
 

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ
የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ