ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል — ሉቃ 3:16

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡

የአስተዳዳሪው መልዕክት

ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት ማቴ. ፫፥፪፣ ማር. ፩፥፪፣ ሉቃ. ፫፥፫

መንግሥተ ሰማያት በልጅነት፤ ልጅነት በሃይማኖት ልትሰጥ ቀርባለችና እመኑ፤ ንስሐ ግቡ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

ውድ አንባቢያን በቅድሚያ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስም በአሜሪካ ሀገር የመጀመሪያ ወደ ሆነው ወደ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያን ድረ ገጽ እንኳን ደህና መጡ፡፡ አገልግሎቱን በእውን ለማየትና ለመገልገል የቻልነውንም እንኳን ለዚህ አበቃን እላለሁ፡፡

የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያነሳሳቸው ካህናት፣ ምዕመናንና ምዕመናት ተሰባስበው ሲመካከሩ ከቆዩ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ለመትከል በመወሰናቸው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ የተተከለ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የተተከለው በሜሪላንድ ግዛት በሞንትጎሞሪ ክልል ማለትም በራክቪል፣ ጌተርስበርግ፣ ኦልኒ፣ ጀርመን ታውን፣ ክላርክስበርግ፣ ፖቶማክ፣ ሲልቨርስፕሪንግ፣ ወዘተ. አካባቢ የሚገኙ ምዕመናን በቦታ ርቀት ምክንያት ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ለመሄድ ባለመቻላቸው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙና የምሥጢራት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡

ሐመር/መርከብ አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የክርስቶስ አካል የሆኑትን ልጆችዋን ማለትም ሕዝበ ክርስቲያንን ማዕበል፣ ሞገድና ነፋሳት ከበዛበት ዓለም ባህር አጓጉዛ ገነት መንግሥተ ሰማያት ታደርሳለችና፡፡ ብርሃን የተባለውም መድኅነ ዓለም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የባህረ ሃሳብ ትምህርት

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በመለአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ተብለው ከሚታወቁት ከካህኑ ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ የተወለደ ሲሆን በወንጌል እንደተጻፈው መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ ያስተምር ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፪ መጥምቁ ዮሐንስ በነብዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም፤ በምድረ በዳ የሚያስተምር የአዋጅ ነጋሪ ቃል ኢሳ. ፲፩ ፥ ፩ ተብሎ የተነገረለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምና በዮርዳኖስ አውራጃ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፡፡ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ሁሉም በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፮

ከሰዱቃውያንና ከፈሪሳውያን ወገን መጥተው ሲጠመቁ አይቶ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ ትሸሹ ዘንድ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህስ ለንስሐ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ፡፡ አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ .........ምሳር በዛፎች ግንድ ላይ ሊቆርጥ ተዘጋጅቷልና መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፱ ጥምቀቱንም በተመለከተ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከእኔ አስቀድሞ የነበረ ነው ከእኔ ይበልጣል፤ እርሱ በእሳት ያጠምቃችኋል፤ የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፲፩ እያለ ያስተምር ነበር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በብሕትውና በበረሃ/በገዳም የኖረ፣ የብሉይና የሐዲስ መሸጋገሪያ፣ የመጨረሻው ነቢይና የመጀመሪያው ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም ማቴ. ፲፩ ፥ ፲፩ ተብሎ በጌታ የተመሰከረለት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከዕረፍቱ በኋላ ብዙ ቃል ኪዳን የተሰጠው መሆኑ በገድሉ በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንም በየቦታው በቃል ኪዳኑ ሲጠቀሙ በመኖራቸውና እየተጠቀሙ በመገኘታቸው ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ በነፍስም በሥጋም ብዙዎች ፈውስን አግኝተዋልና፡፡

እኛም በዚህ በትንቢቱ ፍጻሜ ዘመን ላይ የምንገኝ በሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት የሚከተሉትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠትና ሐዋርያዊ ተልዕኳችንን ለመወጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ እነዚህም፦

 1. ወንጌልን በመስበክ ኃጢአት በሰለጠነበት በዚህ ዘመን ይልቁንም ሥጋዊውን ፍላጎት ለሟሟላት እየባከነ በኃጢአትና በበደል ርቆ ያለውን ሁሉ በንስሐ ሕይወት መጥራትና ለሥጋ ወደሙ ማብቃት፤
 2. በንስሐ ለሥጋ ወደሙ የበቃውንም ምግባር ትሩፋትን በመሥራት ሃይማኖቱን በተግባር የሚገልጽ ክርስትናን በሕይወቱ የሚያስተምር እንዲሆን መርዳት፤
 3. እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሁሉም ዓይነት የሰው ዘር በቀለም፣ በቋንቋ ሳይለዩ ሃይማኖት አልባ የሆነ ያለውን ዓለም ጥቁር አና ነጭ አሜሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ፣ ወዘተ በማስተማር ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና እንዲያገኝ ማድረግ፤
 4. ካህናትም ሆነ ምዕመናን የእውነት ምስክርነት የሚሰጡ፤ እውነትን ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንዲመሰክሩ፤ እንዲገስጹ፤ በይሉኝታና በውዳሴ ከንቱ ሳይጠራሩ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን የእውነት ምስክሮች እንዲሆኑ ማድረግ፤
 5. ሕዝበ ክርስቲያኑ ነፍሱን እንዲያድን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ታንጾ እንዲኖር፤ ትውልዱ ኦርቶዶክሳዊ የተዋሕዶ ሃይማኖትን እንዲኖረውና ኦርቶዶክሳዊነት በዓለም እንዲስፋፋ ማድረግ
 6. ሕጻናትና ወጣቶች ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን አውቀው እንዲረከቡ ማድረግ
 7. በእግዚአብሔር ህግ በቀኖና ወይም በህገ ቤተ ክርስቲያን የምትመራ፣ በቃለ ዓዋዲ መሠረት የምትደዳደር፣ ግልጽና ዘመናዊ አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሠራር ያላት የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን በመመሥረት አብነት የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን
 8. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ባለው ቃል ኪዳን በሥጋ ቁስልና ደዌ በመንፈስና በአጋንንት አሽክላ ተይዘው ለሚሰቃዩ ወገኖች የጸበል አገልግሎት መስጠት
 9. ለትምህርተ አበ ነፍስ ትኩረት በመስጠት በተለይም የምክር አገልግሎት መስጠት

ውድ አንባብያንና በመላው ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህች የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጌታ መንገድ ጠራጊና ቃለ ዓዋዲ ተብሎ በተጠራው በቅዱስ ዮሐንስ ስም ተሰይሞ የእግዚአብሔር ቃል በመዝራት ዘርና ቀለም ሳይለይ እንዲድን፤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን የፈጽማል። ይልቁንም ተተኪው ትውልድ ሃይማኖቱን እንዲረክብ የሚደረገውን ጥረት በጸሎትም ሆነ በሚቻላችሁ ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉልን አደራ እንላለን፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ አምላክ ቃል ኪዳኑን ይፈጽምልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መልዓከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ

መልዓከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ
የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡

መቅደስ ትሠራልኛለህ፡ በመካከላችሁም አድራለሁ፡፡ ዘፀአ. ፳፭፥፰

እግዚአብሔር አምላክ ቦታ የማይወስነው በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚገኝ ቢሆንም በብሉይ ኪዳን ለነብዩ ለሙሴ መቅደስ እንዲሠራለት በማዘዝ በህዝበ እስራኤል መካከል በረድኤት የሚያድር መሆኑን ገልጿል፡፡ ስለ ቤተ መቅደሱም አሠራርና ይዘት ለሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በፆምና በጸሎት አሳይቶታል፡፡ ቤተ መቅደሱንም በተራራው ላይ ባሳየው ምሳሌ መሠረት እንዲሠራው አስጠንቅቆታል፡፡ ዘፀአ. ፳፭፥፱

1. ቤተ መቅደስ በብሉይ ኪዳን

ደብተራ ኦሪትን እንዲተክል እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ጊዜ ጀምሮ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በእስራኤላውያን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ትልቁንና ዋናውን ቤተ መቅደስ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም እጅግ በተዋበ አሠራር አርባ ዓመት በመገንባት ያሠራ ሲሆን እስራኤላውያን ሌሎች አነስተኛ ቤተ መቅደሶችን ምኩራብ በሚል ስያሜ በየመንደሩ ይሠሩ ነበር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ወደ ናዝሬት ገሊላ ተልኮ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ያበሰራት በናዝሬት በሚገኘው ቤተ መቅደስ ነበር፡፡ ሉቃ. ፩ ፥ ፳፩

2. የቤተ መቅደስ ክብርና ጸጋ

የቤተ መቅደስ ክብርና ጸጋ ትልቅና ከእያንዳንዱ ሰው መኖሪያ ቤት እንደሚበልጥ እግዚአብሔር ለነብያቱ እንዲህ በማለት ገልጿል፡፡ ይህንን ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው፤ ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር፡፡ ሐጌ. ፪ ፥ ፯

3. ቤተ መቅደስን ማገልገል ምን ጥቅም አለው?

እግዚአበሔርን ማገልገል ብዙ በረከት፣ ጸጋና ሠላም የሚያሠጥ መሆኑን በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት የምናነበው ሲሆን በተለይም ቤተ መቅደሱን ከፍ ለማድረግ ለሚሠራ ሰው የሚሠጠውን ሠላም እንዲህ በማለት ገልፆታል፡፡ ይህን ቤተ መቅደስ ከፍ ለማድረግ ለምትሠራ ሰውነት ሁሉ ሰላምን እሰጣለሁ፡፡ ሐጌ. ፪ ፥ ፰

4. ቤተ መቅደስ በማን ስም ይጠራል?

እግዚአብሔር አምላክ ቤተ መቅደሱ የወዳጆቹ የቅዱሳን ሥም መታሰቢያ እንዲሆን ስለፈቀደ ቅዱሳት መካናት ሲታነፁ በቅዱሳን ሥም ይጠራሉ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ በማለት በነብያቱ አፍ ተናግሮአል፡፡ ሰንበታቴን የሚጠብቁትንና የማያረክሱትን፥ በቃል ኪዳኔም ጸንተው የሚኖሩትን ሁሉ፥ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአህዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና፡፡ ኢሳ. ፶፮፥ ፯

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ፡፡ ኢሳ. ፶፮፥ ፭

5. ምን እናድርግ?

ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ሚክ. ፫ ፥ ፯

አስቀድሞ ለሙሴ በኋላም ለነብያትና ለቅዱሳን ሁሉ እንደተነገረው አባቶቻችንም ህጉንና ትዕዛዙን ጠብቀው እንደተጓዙት ሁሉ በአከባቢያችንና በመኖሪያችን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ (ቤተ ክርስቲያን) መትከል፣ ከፍ ከፍ ማድረግና ማገልገል ይገባናል፡፡ ሰው እግዚአብሔርን የሚድስና የሚያገለግል ቢመስለውም ቅድስናውና አገልግሎቱ ለራሱ ነው፡፡ በመሆኑም አጥቢያ አብያተ ከርስቲያናትን በመመሥረት፡ -

ሀ. እግዚአብሔር በረድኤትና በጸጋ በመካከላችን እንዲኖር እናደርጋለን፤

ለ. በሰንበትና በቅዱሳት በዓላት ቅዳሴውን እናስቀድሳለን ምሥጢራትን እንሳተፋለን፤

ሐ. ልጆቻችን ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንዲማሩ እናደርጋለን፤

መ. የክርስትናን ሕይወት በቃልና በኑሮ ለሌላው ሕዝብ እናስተምራለን፤

ሠ. ከቅዱሳን በረከት፣ ረድኤትና አማላጅነት እናገኛለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፡፡ ማቴ. ፲፩ ፥ ፲፩ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ነብያት ነብይ፣ እንደ ሐዋርያት የወንጌል ሰባኪ፣ ካህን፣ ባህታዊ፣ ሰማዕትና ጻዲቅ ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ስም የተመሠረተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራክቪል፣ በጌትስበርግ፣ በፖቶማክና በጀርመን ታውን አካባቢ ተጀምሮአልና ከበረከቱ እንድንሳተፍ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

የጽዋ ማኅበር

ከአባቶቻችን ከተረከብናቸው ትውፊታዊ ሥርዐቶች መካከል አንዱ የጽዋ ማኅበር ነው፡፡ ይህ ሥርዐት በሌሎች ሀገሮች የተረሳ በሀገራችን ግን እስከዛሬ ተጠብቆ የቆየ ትውፊት ነው፡፡

ለኢትዮጵያውያን ክርስትና ሲነገር የምንሰማው ወይም ከመጻሕፍት የምናነበው ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት የማኅበራዊ ኑሯችው ውስጥ በሥራ የሚገለጥ ነው፡፡ ከመገለጫዎቻችን አንዱ ይኸው ትውፊታዊ ሥርዐታችን ነው፡፡ ከአመሠራረቱ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡


የጽዋ ማኅበር ምንድን ነው?

የጽዋ ማኅበር የሚባለው በየወሩ ምእመናን ተራ ገብተው እየደገሱ አብረው የሚሳተፉበትና ለችግረኞችም የሚመጸውቱበት ሥርዐት ነው፡፡ በዚህም በረከት ያገኛሉ፡፡ (መዝ 3፤8) ዋጋቸውም አይጠፋባቸውም (ማቴ 10 42)፡፡

ማኅበሩ የሚደረገው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን መላእክት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት የመታሰቢያ ዕለት ነው፡፡ ይህ ማኅበር በቤተክርስቲያን ዙሪያ እና በምእመናን ቤት በየወሩ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ማኅበርተኞች ከአንድ ጽዋ ጠጥተው ከአንድ መሶብ በልተው የጽዋ እኅት፣ የጽዋ ወንድም ይባባላሉ፡፡ ተሰብስበው የቀረበላቸውን ተሳትፈው እግዚአብሔርን ካመሰገኑ በኋላ ከመካከላቸው ችግር የደረሰበት ካለ እዚያው ተወያይተው ይረዱታል፡፡

የአንድ ጽዋ ማኅበር አባላት ዐሥራ ሁለት ናቸው፡፡ ምክንያቱም በዓመት ውስጥ ያሉት ወራት ዐሥራ ሁለት ናቸውና፡፡ አባላቱ ከበዙም እጥፍና ከዚያም በላይ ሆነው በዐሥራ ሁለት ወሮች ይመደባሉ፡፡


የጽዋ ማኅበር አጀማመር

በሐዋርያት ዘመን ክርስቲያኖች ኑሮአቸውን፣ ገንዘባቸው ምግባቸው፣ ትምህርታቸውና ጸሎታቸው ሁሉ በአንድነት ነበር፡፡ (ሐዋ ሥራ 2÷44-47)፡፡ ይህም ሁኔታ እስከ ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስ ሞት ድረስ ቀጥሏል (ሐዋ 8÷1)፡፡

ከቤተክርስቲያን ታሪክ እንደምንማረው በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት በአንድነት ይኖሩ የነበሩ ከስምንት ሺሕ በላይ ክርስቲያኖች ወደየሀገሩ ስለተበታተኑ እንደቀድሞው በአንድነት ለመመገብና ለመኖር አልቻሉም፡፡ ሆኖም ያንን የፊቱን መልካም ጅምራቸውን ላለመዘንጋት ቢያንስ በበዓላት ቀናት ከየቤታቸው ከየቦታቸው እየተጠራሩ በአንዳቸው ቤት በአንድነት የተገኘውን ይመገቡ ነበር፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ዘንድ የምናየው የጽዋ ማኅበር የዚህ ምልክት ነው፡፡ ይህም ምልክት ከእኛ ዘመን የደረሰው የቀደሙት አባቶቻችን ይህ የክርስትና ምልክት እንዳይጠፋ በሃይማኖት ጸንተው በመጠበቃቸው ነው፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን የተረከቡትን አስረክበውልናል፡፡ የወረሱትን አውርሰውናል፡፡ በመሆኑም አባቶቻችን ያቆዩልንን ድንበር ምልክቶች (የሃይማኖት)፣ ሥርዓቶች ሁሉ መጠበቅ፣ ጠብቆም ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ግዴታችን ነው፡፡


የጽዋ ማኅበር ሥነ ሥርዐት

የጽዋ ማኅበር ሥነ ሥርዐቱን ስንመለከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባሕልና ትውፊት እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡

ሙሴው (ሊቀ ማኅበሩ) ከማኅበርተኞቹ መካከል በዕጣ ይመረጣል፡፡ ስያሜውም ሙሴ ይባላል፡፡ ምሳሌነትም አለው፡፡ ሙሴ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለሕዝብ እግዚአብሔር ለእስራኤል ዘሥጋ መሪ መጋቢ እንደነበረ ይህም ለእስራኤል ዘነፍስ ለምእመናን መሪ፣ መካሪ በመሆኑ ስሙን ሙሴ ይሉታል፡፡ ሙሴ መና አውርዶ ዳመና ጋርዶ፣ ውኃ ከደንጊያ አፍልቆ እስራኤልን አርባ ዓመታት እንደመገባቸው፣ ይህም በአገልግሎት ዘመኑ የጽዋ ወንድሞቹንና እኅቶቹን መንፈሳዊ ምክር ይመክራቸዋል፡፡ የፍቅር ምልክት የሚሆን ማዕዱን በክርስቲናዊ ሥነ ሥርዐት ይመግባቸዋልና፡፡

ሙሴ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመግዛት ሳይሆን ለማገልገል እንደተሾመ ሁሉ የዚህም ተቀዳሚ ተግባሩ ወንድሞቹና እኅቶቹን ለማገልገል በዕጣ በፈቃደ እግዚአብሔር ስለሚመረጥ ሙሴ ብለውታል፡፡ ሙሴ የሚሆነው ወንድ ብቻ አይደለም፣ ሴትም ትሆናለች፡፡ ሙሴው ወይም መሴይቱ በድንገተኛ እክል ምክንያት በማኅበሩ ቀን ያልመጣ(ች) እንደሆነ ምክትሉ ተተክቶ ይሠራል፡፡ ይህንንም ግልገል ሙሴ ይሉታል፡፡ ከሙሴው እና ግልገል ሙሴ ጋር ሆነው የሚሠሩ ከማኅበሩ አባላት የተመረጡ ፈቃደኞች ሰዎች ደግሞ ደርገ ሙሴ ይባላሉ፡፡

የሙሴው (ይቱ) ተግባር

- አዲስ አባል ወደ ማኅበሩ ለመግባት በጠየቀ ጊዜ ከማኅበሩ ጋር መክሮ ፈቃድ ይሰጣል፡፡

- ከአባላቱ መካከል የታመመ ወይም ሌላ እክል የደረሰበት ካለ ለማኅበሩ አስረድቶ ርዳታ ይሰበስባል

- በየወሩ ምእመናኑ ሲሰባሰቡ አደግድጎ ቆሞ ያገለግላል

- ምእመናን ወደቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት

የባለተራዎቹን ስም ዝርዝር ባለሳምንት፣ ባለሁለት፣ ባለሦስት ወዘተ. በማለት ማኅበርተኞቹም ተራቸውን ቢያውቁም፣ በፍቃዱ እኔ አለሁ ይላሉ ሙሴው/ይቱ/ ጽዋውን ከፍ አድርጎ ይዞ በማዕከል ይቆምና የሚከተለውን ያውጃል፡- ማነው ባለሳምንት ያስጠመደህ በዐሥራ ስምንት እኔ ነኝ የምትል የዕገሌ ወዳጅ ይላል፡፡

በዚህ ጊዜ ባለተራው ተነሥቶ እኔ አለሁ፣ የዕገሌ ወዳጅ፤ ቢያውለኝ ቢያውላችሁ ማይ ሹሜ ቄጠማ ጎዝጉዤ እጠብቃችኋለሁ ብሎ በማኅበሩ መካከል ይሰግዳል (ይወድቃል)፡፡

በዚህ ጊዜ ቄሱ አለሁ እንዳልክ አለሁ ይበልህ፤ እንደወደቅክ ኃይለ አጋንንትን ይጣልልህ፤ ለቀጠሮ ያብቃን ብሎ አቡነ ዘበሰማያት ይሰጣል፡፡

በሁለተኛው የሁለተኛውን ወር ባለተራ ማነህ ባለ ሁለት ያስጠመደህ በዐሥራ ሁለት እኔ ነኝ የምትል የዕገሌ ወዳጅ ይላል፡፡ ሌላው አይለወጥም እንደመጀመሪያው ነው፡፡

ባለተራው በአጋጣሚ ያልመጣ ቢሆን እንኳን ወኪል ይልካል፣ ያለዚህ ግን ወንበር ገፊ የሆነውን እኔ አለሁ ብሎ ተመርቆ ጽዋውን ይወስዳል፡፡ ሁሉም ካልተገኙ ሙሴው ይመረቃል፡፡ ማኅበሩ ግን ባለተራው ይከፍላል፡፡ ባለተራው በተለያዩ ምክንያቶች መክፈል ያልቻለ እንደሆነ ግን ያስተላልፉለታል፡፡ ለዚያም አዋጥተው ይከፍሉለታል፡፡

አራተኛው ባለተራ ስሙ አይጠራም፤ እሱም እኔ ነኝ ብሎ አይነሣም፤ ሙሴው ግን ባለ አራት ቤትህን አትሳት፤ ተጠራጠር፤ ብቅል ስቀል ብሎ በሽፍን ያስታውቀዋል፡፡

ዐዋጁና ተራ መንገሩ ሲፈጸም ሙሴው እንደቆመ በራሱ ለደርገ ሙሴውና በደገሰው ወንድም ስም ሆኖ የሚከተለውን በመናገር ማኅበሩን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡

ለሙሴ ለደርገ ሙሴ ዐይኑ በሳሳ፣ እጁ በዱላ፣ ባለቤት ጠላው በቀጠነ፣ ቆሎው ባረረ፣ ዳቦው በቀነበረ ማሩን ይላሉ ብሎ ከተናገረ በኋላ እሱም፣ ግልገል ሙሴውም ባለቤቱም በማኅበሩ ፊት ይሰግዳሉ (ይወድቃሉ)፡፡

በዚህ ጊዜ ማኅበሩ በሙሉ ተነሥተው ባንድ ድምጽ ሙሴው ዐይኑ አልሳሳም፤ እጁ አላዳላም፤ ባለቤት ጠላው አልቀጠነም፤ ወይነ ቃና ነው፤ ዳቦውም አላረረ ኅብስተ መና ነው፤ ወሰው ወሰው፤ እንዲህ ያለ የለም ብለው ደስታቸውን በጭብጨባ በዕልልታ ይገልጻሉ፡፡ ቄሱም መርቆና አሳርጎ ሁሉም ወደየቤታቸው ይሔዳሉ፡፡ እያንዳንዱ ባለተራ ለጻድቁ ወይም በቅዱሱ ስም ከጠበሉ በጽዋው፣ ከኅብስቱ በመሶብ ወርቅ አድርጎ እየተሸኘ ወደ ቤት ይሔዳል፡፡


ማጠቃለያ

የጽዋ ማኅበር ከሐዋርያት የተገኘውን አብሮ የመብላት ትውፊት በመያዝ በእግዚአብሔር፣ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን መላእክት በጻድቃንና በሰማዕታት ስም በአንድነት በመገናኘት የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ የቅዱሳንን የተጋድሏቸውን ነገር እያሰቡ በክርስቶስ አንድ በመሆናቸው ያገኙትን ፍቅር ለማጎልበት ቤተክርስቲያን ወይም በመኖሪያ ቤታቸው ተሰባስበው ከአንዲት ጽዋ በመጠጣት ከአንድ መሶብ በመብላት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን የሚወጡበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ከላይ በተገለጸው መሠረት የቅዱሳንን መታሰቢያ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያገኛሉ (ምሳ 10÷7 ማቴ 10÷42)፡፡ የሚዘጋጀውም ጠበል ጸዲቅ የሚባረከው ውዳሴ ማርያም፣ መልከዐ ማርያምና መልከዐ ኢየሱስ ተደግሞ በመስቀል ስለሆነ ልዩ ነው፡፡ ምእመናኑም በእምነት ስለሚበሉና ስለሚጠጡት እየተሳሉ ከበሽታቸው ሁሉ ይፈወሱበታል፡፡

ትውፊተ አበውን አክብረን በሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር የእግዚአብሔር

ቸርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡


በመ/ር ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ

“ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፡፡” ሮሜ 6፡5

በጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ አሳሳችነት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላላፋቸው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ሔዋን ከክህደት የደረሱት በዲያቢሎስ አሳሳችነት በመሆኑና ለሰው ልጆች ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሳ የተፈረደባቸውን ሞት በሞቱ ሊደመስስ ሰው ሆነ፡፡ ዮሐ1፡1 ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ 30 ዓመት ሲሞላው ተጠመቀ፡፡ እንደተጠመቀም ልዋል ልደር ሳይል ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ በዚያም ጾመ ጸለየ በዲያቢሎስም ተፈተነ፡፡ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ሞታቸውን ሊደመስስ፡፡ ዕዳቸውን ደመስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራ ተቀበለ፤ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፣ ምራቅ ተተፋበት፣ ተገረፈ፣ በገመድ ታስሮ ተጎተተ፣ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ በደል ደመሰሰ፡፡ ሞት ድል ተነሳ፡፡ ማቴ. 27-28

ይህንን የቤዛነት፣ የነጻነትና የድል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም ከጾሙ በኋዋላ መከራውን ስቃዩን ከሆሳዕና በዓል ጀምሮ በማሰብ፤ በጥንተ ጠላታችን አማካኝነት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርደህ፣ ቢገርፉህ፣ እርቃንህን ቢያደርጉህ፣ ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን “ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡ አማኑኤል አምላኪዬ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡ ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡ ኃይሌ መከታዬና ረዳቴ ለሆንከው ለአንተ ለአምላኬ አማኑኤል ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ጽናትም ለዘለዓለሙ የአንተ ናቸው፡፡” የሚለውንና በሌሎች የሰሙነ ህማማት ሥርዓቶች አማካኝነት እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ ቅዱስ ጳውሎስ በፊል. 3፡10 ላይ እንደጠቀሰው “እርሱንና የትነሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራወም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንደመስለው እመኛለሁ፡፡” እንዳለው እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ ጸጉራቸውን ተላጭተው የአምላካቸውን መከራ ያስባሉ፡፡ “ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያናቸው ለመስማት በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ትንሣኤውም ይበሰርላቸዋል፡፡ “ጌታ በእውነት ተነሥቷል፡፡” እያሉ ይመሰክራሉ፡፡

ትንሣኤው የድህነት ብሥራት በመሆኑ ለሃምሳ ቀናት ያህል ብሥራቱ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ ወዘተ. ይዘከራል በማንኛውም ቦታም ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን … እየተባለ ሞት መደምሰሱን ነጻነት መታወጁን በሰላምታ ይበሠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ነጻነት በተለያየ ይገልጹታል፡፡ በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ አባት ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፡፡ /እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት 5፥1/እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፣ ሙታንንም አስነሣ፤ እንደተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደዘበቱበት፣ እንደሰደቡት፤ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ሁሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፡፡ /ቅዱስ ሄሬኔዎስ ሃይ. አበ. 7፥28-31/ እንዲህ ሰው ሆኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፤በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ /ዘሠለስቱ ምዕት 19፥24/

ሞትን ያጠፋው፤ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፤ሰው የሆነ፤ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ ሰው የሆነ አምላክ ነው እንጂ፤ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ /ቅዱስ አትናቴዎስ ሃይ. አበ. 25፥40/

ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ /ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ/የብረት ቁልፎቿም ተቀጠቀጡ /ፍዳመርገም ጠፋ/፤ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፡፡ /ዝኒ ከማሁ 26፥20-21/

ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፤ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መሆን ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጉድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፤ ይህስ እውነት ከሆነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፤ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበስር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፤ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትሆን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋ ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ፡፡ አባቶቻችን ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ ብለው አስተማሩን፤ ይህንን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፡፡ /ዝኒ ከማሁ 30፥31-36/

አሁን እግዚአብሔር ሞተ ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፤ ሞት የሌለበት ባይሆንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፡፡ /ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 34፥17-18/

ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፤ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ 36፥30/

በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፤ ፍሬውንም /ሥጋውን፤ ደሙን/ ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወደ አልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደነበረው መዓርግ ደረስን፤ ክፉውንና በጎውን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፡፡ /ዝኒ ከማሁ 36፥38-39/

የሕይወታችን መገኛ የሚሆን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደለወጠ እናምናለን፤ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደተጻፈ፡፡ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው? ብሎ እንደተናገረ፡፡ /ቅዱስ አቡሊዲስ ሃይ. አበ. 42፥6-7/

በመለኮትህ ሕማም ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልክ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መሆንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደመሆንህ በፈቃድህ የሞትክ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፤ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፤ ከሙታን ጋር የተቆጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት፤ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ሁሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፡፡ /ቅዱስ ኤራቅሊስ 48፥12-13/

እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ በሥጋ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፤ የሰውን ወገኖች ሁሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያለመለወጥ ሁል ጊዜ ይኖራል፤ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደተነሣ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም ሃይ. አበ. 52፥11-12/

የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይልን እንጂ፤ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. 53፥27/

መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ መለኮት የሥጋ ሕይወት በምትሆን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፤ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፤ በዝግ ቤት ገብቷልና፤ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፤ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሃይ. አበ. 56፥37-38/

ክርስቶስ የሙታን በኲር እንደምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዐዛርን በሞተ በዐራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ሆነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኲር ነው፤ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ. 57፥3-6/

ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፤ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ሃይ. አበ. 60፥29/

ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፡፡ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞትነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የሆነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት /እትራት/ አላጠፋምና፡፡

በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. 66፥7-12/

በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፡፡ /ቅዱስ ቄርሎስ ሃይ. አበ. 72፥12/

ሕማምን ሞትን ገንዘብ አደረገ፤ በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕ ርይ በመዋሐዱ ነው፤ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመሆን ሥራ ነውና፤ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመሆን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትን፤ ትንሣኤን/ እናውቃለን፡፡ /ዝኒ ከማሁ 72፥35/

በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደሆነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፤ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፡፡ /ዝኒ ከማሁ 79፥9/

የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን /ኃጢአትን/ ሻረ፤ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ /ፍዳ መርገምን አጠፋ/፤ ሲኦልን በዘበዘ፤ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፤ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለሁሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚሆን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 83፥6/

ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤እንደተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደሆነ፣ መድኀኒታችን በሚሆን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደሰጠን እናምናለን፤ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ሁሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ሁሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከሆነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከሆነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፤ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደመሆኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደመሆኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፡፡ /ቅዱስ ሳዊሮስ ሃይ. አበ. 84፥18-20/

ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪሆን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፤ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ሃይ. አበ. 90፥34/

ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ፤ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፤ እንደሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፤ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣን ገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፤ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለሆነ በሥራው ሁሉ አይለወጥም፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 92፥15/

ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ሁለንተናው እሳት እንደሆነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፣ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ /መቀጥቀጫ/ ላይ እንዲሳብ /እንዲቀጠቀጥ/፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ፣ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደሆነ ዕወቅ፡፡ በዚህ ትንሽ ምሳሌ፤ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፤ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስን መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፤ ይህንም የሚያስረዳ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፡፡ /ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 96፥50-52/

ዳግመኛ እርሱ እንደሞተ በሦስተኛውም ቀን እንደተነሣ፣ ስለተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ሆኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ሁሉ አንድ ሆኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፤ ለሁሉም እንደሥራው ይከፍለዋል፤ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሃይ. አበ. 99፥32/ በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፤ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፤ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፤ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታን በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፡፡ /ቅዱስ ፊላታዎስ ሃይ. አበ. 105፥14/

በሞቱ ሞትን ያጠፋው እሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፣ ለሁሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፤ ለሁሉ አምላክነቱን አስረዳ፤ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፤ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ 111፥13/

እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱ ንከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፤ እርሱ ራሱ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም አትንኪኝ አላት፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፡፡ /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ 95/

ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለነፍስና ያለሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ ብሎ እንደተናገረ፤ አይሁድም ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ትላለህ አሉት፤ ይህንንም የተናገረው ስለራሱ ሰውነት ነው፡፡

በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፤ ሁለተኛም ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ፡፡ ዳዊትም አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ይላል፡፡ ነቢዩ አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከሆነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድነው? /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ 77-79/

ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፡፡ /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ 1፥29-31/

ሰውን ስለመውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፡፡ /ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ 1፥24/ በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፤ የተወጋውን ጎኑን፤ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የሆነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፡፡ /ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት 4፥25-27/

ሰማያት /ሰማያውያን መላእክት /የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት /ቅዱሳን/ የደስታን በዓል ያደርጋሉ፣ ምድር /ምድራውያን ሰዎችም/ በክርስቶስ ደም ታጥባ /ታጥበው/ የፋሲካን በዓል ታደርጋለች /ያደርጋሉ/ ያከብራሉ /ታከብራለች/፡፡

ዛሬ በሰማያት /በሰማያውያን መላእክት/ ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኩር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ሁሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፡፡ /ድጓ ዘፋሲካ/

መጋቢት 29ቀን 2010 ዓ.ም.

በመ/ር ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ

ጸሎተ ሐሙስ


ጸሎተ ሐሙስ ነቢያት በሀብተ ትንቢት፤ በመንፈሰ ትንቢት እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት /መዝ. 117፥24/ በማለት ትንቢት የተናገሩላት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ትላልቅ የተባሉ ምሥጢራት የተፈጸሙባት ዕለት ናት፡፡

እግዚአብሔርም በግብጽ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው ይህ ወር የወሮች የመጀመሪያ ይሁናችሁ የዓመቱም የመጀመሪያ ወር ይሁናችሁ፡፡ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ፡፡ የቤቱ ሰዎች ቁጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደነፍሶቻቸው ቁጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ፡፡ የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰዱ በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፡፡ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ ከመራራው ቅጠል ጋር ይበሉታል ጥሬውን በውኃ የበሰለውን አትብሉ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት ከእርሱም እስከ ጧት አንዳች አታስቀሩ እስከ ጧትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ በትራችሁንምበሚፈጽሙበት በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፡፡ ፈጥናችሁም ትበሉታላችሁ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው፡፡ እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ አገር አልፋለሁ ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ ለልጅ ልጃችሁም ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ /ዘዳ.12፥1-15/፡፡ እስራኤል ይኸንን ሥርዓት ዓመታዊ በዓል ዋዜማ ላይ ነበር:: ሐዋርያቱ ወደ ጌታችን ቀርበው እንዲህ አሉት ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ? እርሱም ወደ ከተማ ወደ አልዓዛር ቤት ላካቸው /ማቴ.20፥6-18/፡፡ አስቀድመን የገለጥነው ቃል እስራኤል ዘሥጋ ከሞተ በኩር የዳኑበት የፋሲካ በግ ምሳሌነት የሚያሳይ ነው፡፡ በጉ ነውር የሌለበት የመሆኑ ምክንያት ኀጢአት የሌለበት የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉን በወሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን እንዲሠውት እንደታዘዙ የጌታ ምክረ ሞቱ በዐሥር ተጀምሮ በዐሥራ አራተኛው ቀን ተፈጽሟል፡፡ የበጉ ደም የተቀባበት ቤት ሞተ በኩር አልደረሰም በመስቀሉ ላይ የፈሰሰውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ክርስቲያኖችንም ሞት አይደርስባቸውም፡፡ የበጉን ሥጋ ጥሬውንና ቅቅሉን እንዳይበሉ ጥብሱን እንዲበሉ ታዘዋል ይህም በእሳት የተመሰለ መለኮት የተዋሐደውን ነፍስ የተለየውን ሥጋና ደም ለምንቀበል ለእኛ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ነው፡፡

አታሳድሩ ከአንዱ ወደ ሌላው አትውሰዱት መባሉ ጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ላለማደሩ እና ወደ መቃብር መውረዱን የሚያስረዳ ሲሆን፤ የበላችሁትን አታሳድሩ መባሉ ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ተረፈ መሥዋዕት አያድርምና ነው፡፡


በጸሎተ ሐሙስ የሚከተሉት ዋና ዋና ምሥጢራት ተፈጽመዋል፡-


የማይሻረው፣ ዘላለማዊው፣ ፍጹሙ፣ ኪዳን የተመሠረተበት ዕለት ነው፡፡

እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ኪዳናት የተሻሩ አሉ፤ የማይሻሩም አሉ፡፡ የማይሻሩ ኪዳናት ኪዳነ አዳም፣ ኪዳነ ሙሴ፣ ኪዳነ አብርሃም፣ ኪዳነ ዳዊት፣ ኪዳነ ምሕረት ናቸው፡፡ የተሻሩት የደም ኪዳናት ናቸው፡፡ በደም የተመሠረቱ የብሉይ ዘመን ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን አምላካዊ ደም ተሽሯል፡፡

በዚች ዕለት በአልአዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጡ፡፡ ከኅብስቱ ከፍሎ አማናዊ ሥጋ፤ ከወይኑ ከፍሎ አማናዊ ደም አድርጎ ባርኮ ቀድሶ አክብሮ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ /ማቴ.26፥26/ ይህ ሥርዓት የክህነቱንም ሥርዓት የቀየረ ሥርዓት ነው፡፡

ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞች የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል፡፡ እርሱም አስቀድሞ ስለ ራሱ ኀጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ አይገባውም፡፡ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህንን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና /ዕብ.7፥27/ ተብሎ የተነገረለት የሐዲስ ኪዳን የክህነት ሥርዐት ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ የነበረው የእንስሳት ደም ተሽሮ አማናዊ የሆነው የክርስቶስ ደም የተተካበት ዘላለማዊ ፍጹም ኪዳን የተቀበልንበት ዕለት ነው፡፡


አዲስ ሕይወት አዲስ ዘመን የተመሠረተበት ነው፡፡

ዘመኑ ሥያሜውን ያገኘው በዚች ዕለት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ሥርዓት መሥዋዕት የተሠራበት ዕለት ነው፡፡ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራ አንሥቶ ባርኮ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ማቴ. 26፥26 ስለዚህ ሐዲስ ኪዳን የሚለው ስያሜ በዚች ቀን እንደተፈጸመ ልብ ይሏል፡፡ የቀደመው ኪዳን እርሱም በደም የሆነው መሥዋዕትነት አለፈ በተሻለው የመረጨት ደም እርሱም በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ምክንያት ዘመን ተለወጠ፣ ስያሜውንም አገኘ እርሱም ሐዲስ ኪዳን /ዓመተ ምሕረት/ ነው፡፡ የፍዳ፣ የመርገም፣ የኩነኔ ዘመን አልፎ የምሕረት፣ የነፃነት፣ የድኅነት ዘመን ተተካ፡፡


አገልጋዮቹን የለየበት ዕለት ነው፡፡

የእርሱ ገንዘብ የሆኑ ሐዋርያት እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ይታመኑ ዘንድ አገልግሎታቸውን ያጸናበት የማይገባቸውን ወገኖች የለየበት ዕለት ናት፡፡ ይሁዳ የሐዲስ ኪዳን ሰው አልነበረም በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ፤ ሲበሉም እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ፡፡ እጅግም አዝነው እያንዳንዱ ጌታ ሆይ እኔ እሆንን ይሉት ጀመር፤ እርሱም መልሶ እጁን በወጭቱ ያጠለቀው እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ነው አለ፡፡ /ማቴ.26፥20/ ይሁዳ በዚች ዕለት ከሐዋርየት ተለየ፤ ጌታውን ለሠላሳ ብር አሳልፎ ሰጠ፡፡ ስለዚህ የሐዲስ ኪዳን አገልጋዮች ከፍቅረ ነዋይ፣ ከአድመኝነት፣ ከምቀኝነት የራቁ፣ የተለዩ ለፈጣሪያቸውና ለአገልግሎታቸው የታመኑ እንዲሆኑ ሥርዐት ተሠራ፡፡


ሐዋርያት የተጠመቁበት ዕለት ነው፡፡

እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ዐሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ ከራት ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡ ዮሐ.13፥1-10

ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ሊከላከል ሞከረ፤ ጌታችን እንዲህ አለው እኔ የማደርገውን አሁን አንተ አታውቅም በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው /ዮሐ.13፥10/፡፡ ጴጥሮስ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም ባለው ጊዜ የጌታችን መልስ ይህ ነበር ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ቁ.9/ በእርግጥም ያልተጠመቀ ከጌታ እድል ክፍል የለውም፡፡ እናም ቅዱሳን ሐዋርያት በእዚህች ዕለት የተጠመቁባት ዕለት ናት፡፡


በጸሎተ ሐሙስ የሚከናወን ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ፡፡ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ /ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል፣ ጸሎተ እጣን ይጸለያል፣ ቤተ ክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል፡፡

ዲያቆኑ ሁለት ኩስኩስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል አንዱ ለአግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ጸሎተ አኮቴት የተባለ የጸሎት ዓይነት ተጸልዮ፣ ወንጌል ተነቦ ውኃው በሊቀ ጳጳሱ /በካህኑ/ እጅ ተባርኮ የሕጥበተ እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን ከወንዶች እስከ ሴቶች ይከናወናል፡፡

ሥርዓተ ሕጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምስጢሩም የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ወይራ ጸኑዕ ነው ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱም በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል ጌታችን በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው፡፡ ማቴ.26፡26

ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው ዮሐ.13፡14፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርተ ቅዳሴው ተከናውኖ ምእመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡


የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ

ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምጽ ነው፣ ደወሉ የጸናጽል ድምጽ ነው በቀስታ ስለሚጮህ፣ የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም፡፡ ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምስጢር ጌታችንን ማስያዙን ለማመልከት ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡

በመቀጠል ክቡር ይእቲ፣ እጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዘዛና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡


ማጠቃለያ

ቅዱስ እግዚአብሔር አማናዊ ሥጋውን፤ አማናዊ ደሙን የሰጠባት፣ ለሕይወት ለበረከት እንድንሆን ምሥጢሩን የገለጠባት፣ ምዕመናንን ቅዱስ ሥጋውን በልተው ክቡር ደሙን ጠጥተው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚቀበሉባት፣ የትንሣኤውን ብርሃን በተስፋ የምንጠባበቅባት ዕለት በመሆኗ ይህች ዕለት ለእኛ ለክርስቲያኖች ልዩ የሆነ ትርጉም አላት፡፡ ዕለቷንም የምናከብረው በዚህ መንፈስ ነው፡፡


በሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ

መጋቢት 10 ቀኖች መስቀሉ ተገኘ

መጋቢት 10 ቀን የመስቀል በዓል የሚከበርበት ዋና ምክንያት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ፈቃድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና በእመቤታችን ፈቃድና (እሺ ባይነት )ሰው ሆኖ ተወልዶ ፤ የሞተውንና የዲያቢሎስ ባርያ የነበረውን የሰው ልጅ ነጻ የሚወጣበት ቀን ሲደርስ፤ የሰው ልጆችን ሞት በሞቱ ሲደመስስ ማዳኛው መሳርያ የነበረው ቅዱስ መስቀል ነው።

ቅዱስ መስቀል የክርስቶስ ፡-መገለጫው ፣ዙፋኑ ፣ታቦቱ(ስጋው የተቆረሰበት ደሙ የፈሰሰበት) ነው። ዲያቢሎስም ምርኮውን በፈቃዱ ለመመለስ የተጠራበት የፍርድ አደባባይ ነው ። በመስቀሉ ዙፋን ላይ ሆኖ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ነጻ ያወጣብትና ለሰው ልጆችም የድል አድራጊነት ምልክት አድርጎ የሰጠው መስቀልን ነው።

ይህ በመሆኑ ዲያቢሎስ ድል ስለተደረገበት፣ አይሁድም የዲያቢሎስ አገልጋይ ሆነው ክርስቶስን ሰቅለው ለመስቀሉም ጠላት ሆነው ሳለ ፤ መስቀለ ክርስቶስ ቅዱስ ስለሆነ በውቅቱ ብዙ ገቢረ ተአምራት ያደርግ ነብር። ሙታን ይነሱ ድውያን ይፈወሱ ነበር በተለይ ከዕርገት ክርስቶስ በኋላ።ድል በተደረገው በዲያቢሎስ ምክር የመስቀሉ ኃይል ያስጨነቃቸው አይሁድ ዓለም መድኃኒት ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል አካሉ ያረፈበት፣ደሙ የፈሰሰበት በመሆኑ ሕሙማንን ሲፈውስ ሙታንን ሲያስነሳ በማየታቸው ስለተጨነቁ "ሰውን ተሰቅሎ እንዲሞት ከመፍረድ ይልቅ የተሰቀለበትን መስቀል መቅበር ይቀላል" ብለው በመምከር መሬት ውስጥ ቀብረው የቆሻሻ መጣያ ቦታ አደረጉት።

መስቀሉ ከተቀበር በኋላ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል አካባቢው ቆሻሻ ሲደፋበት ኖሮ ቦታው ወደ ተራራነት ተለወጠ።

ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ነውና በአራተኛው መቶ ክ/ዘመን የክርስትና እምነት ባለውለታ የሆነችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ልጇን ቆስጠንጢኖስን ከመውለዷ በፊት ልጅ ባለመውለዷ ታዝን ነበርና ስዕለት ተሳለች።

እንዲህ ስትል "እንደነ ሀና እመ ሳሙኤል እና እንደነ ኤልሳቤጥ እመ ዮሐንስ መልካም ፍሬ የሆነ ልጅ ብትሰጠኝ ለዓለም ድኅነት የተሰቀልክበትን መስቀል ከተቀበረበት እንዲወጣ አደርጋለሁ፤ ክቡር የሆነው መስቀልህ የሚያርፍበት ቤተ መቅደስም አሳንጻለሁ፤ በተጨማሪም የምትሰጠኝን ልጅ የሃይማኖት ትምህርት አስተምሬ ከእስጢፋኖስ ሞት ጀምሮ በስደትና በመከራ ላይ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ዋስ ፣ጠበቃ እንዲሆን አደርጋለሁ።" በማለት ተሳለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔርም ጸሎትና ልመናዋን ሰምቶ የተባረከ ልጅ ቆስጠንጢኖስን ሰጣት።

ቆስጠንጢኖስ ተወልዶ አድጎ ንጉሥ እንደሆነ፤ እናቱ የተሳለችውና የሚያስጨንቃት የመስቀሉ ምስጢር ለልጇ ተገለጸ።ታላቅ ተአምር በ312 ዓ/ም ቆስጠንጢኖስ ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ሊዋጋ ሲል እንዴት አድርጎ ጠላቱን ማሸነፍ እንዳለበት በሐሳብ ሲያወጣ ሲያወርድ "በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ታሸንፋለህ "የሚል ጽሑፍ ያለበት የሚያበራ መስቀል በሰማይ ላይ ተስሎ በራእይ ተመለከተ።

በራእይ ያየው መስቀል እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠው ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ በማመን በሰንደቅ ዓላማው ላይ የወርቅ መስቀል አስቀርጾ ከሰራዊቱ ፊት አስይዞ ዘመተ። ወዲያው ሙልቢያ በተባለው በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነስቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ ።

እናቱ ንግሥት እሌኒ በስዕለቷ መሠረት በ327 ዓ/ም ብዙ ሠራዊት አስከትላ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ፈልጋ ለማስወጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች። መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ የሚያመላክታት ሰው ስታፈላልግ ኪራኮስ የሚባል የእድሜ ባለጸጋ ሽማግሌ አግኝታ ጠየቀችው። እርሱም አባቶቻችን ሲናገሩ እንደሰማሁት ያ ተራራ የመሰለውና የከተማው ሰው ለቆሻሻ መድፊያነት የሚጠቀምበት ቦታ ነው ይሉን ነበር በማለት በጣቱ እየጠቆመ አመላከታት።

መስከረም 16 ቀን ካህናቱን እና ሕዝቡን ሰብስባ ደመራ አስደምራ ጸሎትና ምህላ ካስደረሰች በኋላ ዕጣኑን ጨምራ ደመራውን ብታቀጣጥለው የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ እንደ ቀስተ ደመና ወደ ጎልጎታ በመመለስ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ላይ ተተከለ። ኪራኮስ ያመላከተውን ቦታ ትክክል መሆኑን እግዚአብሔር አጸደቀላት።

ሕዝቡና ካህናቱም ጢሱ ሰግዶ ሲያመለክት በማየታቸው "ይኄዋ መስቀል ይኄዋ መስቀል " እያሉ ደስታቸውን በመግለጽ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። ይህንን ቃልነው ዛሬ "እዮሃ መስቀል እዮሃ አበባየ" እያልን የምናከብረው ።

ቅዱስ ያሬድም " አረጋዊ አንግሃ ገይሠ ብእሲ ዘስሙ ኪራኮስ ዘዕጣን አንፀረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል" በማለት የዘመረው ይህንን ነው። ይህም ሲተረጎም ኪራኮስ የተባለው ሽማግሌ ያመለከተውን የዕጣኑ ጢስ ሰግዶ አረጋገጠ። አይሁድ በጎልጎታ የቀበሩት መስቀል ዛሬ ተገኘ ማለት ነው።

በዚሁ ቀን መስከረም 17 ቀን 327 ዓ/ም ቁፋሮውን አስጀምራ በዚሁ ዓመት መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ተገኝቶ ከተቀበረበት ወጣ።የመስቀል ቤትም አስርታለት የኢየሩሳሌምና የየአህጉራቱ ክርስቲያኖች ክብር ሰጥተው እየተማጸኑት ይኖሩ ነበር።

በ614 ዓ/ም የፋርሱ ንጉሥ ኮስርየስ ኢየሩሳሌምን ወርሮ ህዝቡን ማርከ መስቀሉንም ወስዶ በሀገሩ ቀበረው። በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች የመስቀሉ ከኢየሩሳሌም ተማርኮ መወሰድ እያሳዘናቸው እየጸለዩ 14 ዓመታት ቆዩ።

በ628 ዓ/ም በውቅቱ ነግሦ ለነበረው ክርስቲያን ንጉሥ ህርቃል መስቀሉን ከፋርስ ንጉሥ ተዋግቶ ያመጣላቸው ዘንድ ክርስቲያኖች ተማጸኑት። ንጉሡም ሐዋርያት ሰው የገደለ ዕድሜ ልኩን ይጹም ብለው ያስተማሩትን ጠቅሶ አይሆንልኝም አላቸው። ሕዝቡም በዕድሜው ልክ ተከፋፍለው አንድ ሳምንት ጾሙለትና ከኮስርየስ ጋር ተዋግቶ መስቀሉን መጋቢት 10 ቀን 628 ዓ/ም አመጣላቸው።

አባቶች ንጉሡ ስለመስቀል ፍቅር። ሕዝቡ ጾመው ድል ስላደርገ እኛም ዲያቢሎስን ድል ማድረጊያ የዐብይ ጾም መጀመሪያ ሳምንት በህርቃል ስም ሰይመን እንጾማለን።(የመስቀሉ ጥንተ ታሪክ ብዙ ነውና እዚህ እናቁም)።

መጋቢት 10 ቀን 628 ዓ/ም ሁልጊዜ ወርኃ ጾም በመሆኑ በዓል ለማክበር ስለማይመች ቁፋሮው በተጀመረበት በየዓመቱ መስከረም 16እና 17 ቀን እንዲከበር አባቶች ወሰኑ።

መስቀሉ የድኅታችን ምክንያት መስቀሉ ድል ማድረጊያችን ምልክት ሆኗል።መስቀል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጠብ ግድግዳ የተናደበት ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ መንጋ የሆኑበት ፣ ነጻነታችን የታወጀበት ፣ጠላታችን ሞት የተሸነፈበት ፣ዲያብሎስ የተመታበት ፣ሰላማችን የተረጋገጠበት መሳሪያ በመሆኑ (ኤፌ 2፥14-18) ከሃይማኖት ውጭ ላሉ ሰዎች ስንፍና ቢሆንም ለእኛ ግን ኃይላችን ነው (2ኛ ቆሮ 1፥18) መስቀል ኃይላችን ነው ፣ መስቀል ጽንዓ ነፍሳችን ነው፣ መስቀል ቤዛችን ነው፣ መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው ፣አይሁድ መከራው ለኛ አይደለም ብለው ካዱ ፤ እኛ ግን አመንን ፤ ያመንን እኛም በመስቀሉ ኃይል ዳንን"

መጋቢት 10 ቀን የመስቀሉን በዓል እናክብር። ጥንተ ጠላታችንን ዲያቡልሎስን ድል ማድረጊያችን ነውና የእርሱንም ምልክት እንያዝ።

የመስቀሉ ኃይል ከጠላት ዲያቢሎስ ይጠብቀን። በረከትን ረድኤትን ሰላምን ያምጣልን።

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት 10 ቀን 2010

ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሁለት

ሱባዔ ጥቅሙ (ከክፍል አንድ የቀጠለ)

፫. የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብጹን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል (ዘፍ. ፵፩፥፲፬-፴፮፤ ዳን. ፬፥፱፣ ፭፥፬)፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ኾነ በአጠቃላይ ለሕዝቡ ትምህርት በሚኾን መልኩ ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይኾናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይጠይቅዋቸው ነበር፡፡

ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጠው ያስረዱ ነበር (ዳን. ፭፥፳፰)፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጕም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ኾነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል (መዝ. ፰፥፩)፡፡ ከዚህ ቀጥለን የቀደምት አበውን ሱባዔና ያስገኘላቸውን ጥቅም በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፤

ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቍጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለ ምንም ትካዜና ጕስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል (ዘፍ. ፫፥፳፬)፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነትን ከሚቈራርጥ ባሕር ውስጥ በመግባት ለሠላሳ አምስት ቀን (አምስት ሱባዔ) ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ መሐሪው እግዚአብሔርም የአዳምን ፍጹም መጸጸት ተመልክቶ ‹‹በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ፤ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ብሎ የድኅነት ተስፋ ሰጠው፡፡

አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቈጥር፣ አዳምም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለ ነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቈጠረ ‹‹የተናገረውን የማያስቀር፣ የማያደርገውን የማይናገር ጌታዬ፤ እነሆ ‹አድንሃለሁ› ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤›› እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸሩ አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት፤ ለጸሎት ተነሡ፡፡ ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይኹን!››በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡

ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ የያሬድ ልጅ ሲኾን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመኾኑም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን የመልካም ግብር ባለቤት መኾኑ ተመስክሮለታል፡፡ ‹‹ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፭፥፳፪)፡፡ ይህም በመኾኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ (ዑደት) የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል (ዘፍ. ፭፥፳፩-፳፬፤ ሔኖክ ፩፥፱፤ ይሁዳ፣ ቍ. ፲፬)፡፡

ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመሥፈርት የቈጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣ ቍጥሩ) 35 ሲኾን 35 በ19 ሲበዛ ውጤቱ 685 ዓመት ይኾናል፡፡ 685ን በ12 ስናባዛው ደግሞ 7980 ይኾናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለ ክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ 7510 ይኾናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 2010 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቈጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይኾናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቍጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን (7510) ስንቀንስ 470 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊኾን 470 ዓመት ይቀረዋል ማለት ነው፡፡

ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መኾንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔም ቈጥረዋል (መዝ. ፵፱፥፫፤ ኢሳ. ፯፥፲፬፤ ዘካ. ፲፫፥፮፣ ፲፬፥፩)፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባዔ በአነጋገርና በአቈጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ይለያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር፣ ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመኾኑ ነው፡፡ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በተነሡበት በነቢያት ተናገረ፤›› (ዕብ. ፩፥፩)፡፡ የአቈጣጠር ስልታቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ክርስቶስ ነው፡፡

ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ ከትንቢቶቹ መካከልም፡- ‹‹ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መኾኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንደዚሁም ‹‹እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነጽ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነጻለች፤ በኋላም ትፈርሳለች፤››በማለት የብሉይ ኪዳንን ማለፍና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት ተናግሯል፡፡ የዳንኤል የሱባዔ አቈጣጠር ስልቱም በዓመት ሲኾን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቍጠር ነው፡፡ ይህም ‹ሱባዔ ሰንበት› ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቈጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት ድረስ 490 ዓመት ይኾናል፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣው) ሰባት ስለኾነ ሰባትን በሰባ ብናባዛው 490ን እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቈጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ ክርስቶስ መወለዱን ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የኾነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀውን የማቅረብ፣ የረቀቀውን የማጉላት ጸጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መኾኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ዅሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011 – 971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መኾኑ ብዙ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ ይኸውም ‹ቀመረ ዳዊት› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኀለፈት፤ ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን ናት፤›› (መዝ. ፹፱፥፬) የሚለውን ኃይለ ቃል መምህራን ሲቈጥሩት 1140 ዓመት ይኾናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደ ኾነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቍጠሪያ (መሥፈሪያ) ኾኖ አገልግሏል፡፡ 1140 በ7 ሲባዛ 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

ምንጭ ማኅበረ ቅዱሳን (ነሀሴ4 2007)

ይቆየን

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

የካቲት 14 ቀን 2010

እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል አደረሰን::

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ተአምራት እንደሰራና ብርሃነ መለኮቱን የገለፀ, ትንቢት እንዴት እንደተፈፀነመና አዕማደ (የምስጢር) ሐዋርያት ለምን እንደተመረጡ? ተምረናል::

ዛሬ ደግሞ ከተራራው ግርጌ እነማን ነበሩ? ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ከብሔረ ሙታን ሙሴንና ከብሔረ ህያዋን ኤልያስን አምጥቶ ነበር:: ለመሆኑ ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ? እና የደብረ ታቦር ምሳሌነት ምን እንደሆቱ ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን እንደሚከተለው ቀርቧል::

1. ከተራራው ግርጌ

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ እነሱም ጌታን በ 30ብር የሸጠው የአስቆሮቱ ይሁዳን ጨምሮ የጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፣ ቶማስ፣ ፊልጶስ፣ማቴዎስ፣ በርቴለሜዎስ፣ ስምኦን፣ ታዴዎስ እና ሌላኛው ያዕቆብ ወ/እልፍዮስ ናቸው:: ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህማን ይኖራል” /መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡ “የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡


2. ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?

ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥቷል፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብለው የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ በማቴ.16፡14 ላይ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።” ይላልና፡፡ ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ስለተነገረለት /ዘጸ.33፡23/ ኤልያስ “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡


3. የደብረ ታቦር ምሳሌነት

 • የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡ በጣም ያስቸግራል፤ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ተራራውን ጨርሰው ከላይ ሲወጡ ግን አባጣ ጎባጣውን ሜዳና ገደሉን ያሳያል፡፡ ወንጌልንም በሚገባ ከተማሯት ጽድቅን ከኃጢአት ለይተን እንድናውቅ ታደርገናለች፡፡
 • ለቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በደብረ ታቦር ምስጢረ ሥላሴ እንደተገለጠ በቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ይነገርባታል፡፡ ተራራ መሠረቱ ከመሬት አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ ቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር ሲሆን ራሷ በሰማይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ የተጠሩት ከምድር (ከዓለም) ሲሆን ክብራቸው ግን በሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› እንዲል /ፊልጵ. 3፥20/፡፡

የደብረ ታቦር ተራራ ይህን ሁሉ ምስጢር የያዘ በመሆኑ በክርስትና ታሪክ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮት የተገለጠበት፣ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላትም አንዱ ነው፤ በምእመናንም ዘንድ ቡሔ ይባላል፡፡ የቡሔ በዓል ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ የያዘ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ልናከብረው ይገባናል፡፡


በቀጣይ....

ቡሄ ምን ማለት ነው? ጅራፍ ችቦና ሙልሙል ከባህላዊ ትውፊቱ ባሻገር ሐይማኖታዊ ዳራው ምን እንደሚመስል የምንዳስስ ይሆናል::

1. ቡሄ

ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡

ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም “ቡኮ/ሊጥ” ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “ሙልሙል” የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡


2. ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ እና ጅራፍ ማጮኽ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፋቱንና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምስክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡

የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኅበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡


3. ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የት መጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡ የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡


4. ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን “ቡሄ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ አለ፡፡ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት “የምሥራች” ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ….” ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከእነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምሥጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምሥጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ “ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ” ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ቤተክርስቲያን የምሥጢር ግምጃ ቤት ናት፤ የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፋ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሽ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ-ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤

ብርሃነ መለኮቱን እንደገለጠ ለኛም ምስጥርን ይግለፅልን። የከርሞ ሰው ይበለን:: አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ምንጭ ዲሻሎም

ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

ይህ ሱባዔና ስርዓቱ በሚል የቀረበው ጽሑፍ በ2007 እና 2009ዓ.ም www.eotcmk.org ለፍልሰታ ሱባዔ የተጻፈና የተነበበ ሲሆን አሁንም ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ፍልሰታ ጾምን የሚጾሙበት፣ ሱባዔ የሚገቡበት ጊዜ ነውና ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ሱባዔ ምንድን ነው?

‹ሱባዔ› በሰዋስዋዊ ትርጕሙ ‹ሰባት› ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጐም አንድ ሰው ‹‹ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ ጋር እገናኛለሁ›› ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቍጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቍጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቍጥርን ፍጹምነት ያመለክታል (ዘፍ. ፪፥፪፤ መዝ. ፻፲፰፥፷፬)፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ደግሞ ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ሱባዔ መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መላእክት ለአዳም የጊዜያትን ስሌት አስተምረውት ነበር (ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ)፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል (መጽሐፈ ቀሌምጦስ፣ አንቀጽ አራት)፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ሕሊናው ይወቅሰዋል፤ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሕሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ጉዳይ፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ ‹‹ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ? ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ. ፯፥፳፪፥፳፭)፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ የትካዜ ሸክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ሰው በትካዜ ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይኾንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ (ሱባዔ) ይገባል፡፡ ሱባዔ የሚገባውም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፤

፩. እግዚአብሔርን ለመማጸን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማጸን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅጽኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው (የምንማጸነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና፣ ወዘተ. ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ፈጣሪውን በጸሎት ይማጸናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ኾነ በአገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፡፡ መልሱ ሊዘገይም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት ይጠበቃል፡፡ ‹‹ለምን ላቀረብኹት ጥያቄ ቶሎ ምላሽ አልተሰጠኝም?›› በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለውና፡፡

ከዚህ ላይ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይን ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አኃው (ወንድሞች) ለተልእኮ በወጡበት ወቅት አንዱን ድቀት አግኝቶት ያድሯል፡፡ በነጋታው ‹‹ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ዓለሙን መስዬ እኖራለሁ›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን›› ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው አንድ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ‹‹ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከ፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ››የሚል ድምፅ አሰምቶታል (ዜና አበው)፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ (ሰባት ቀን) እንደ ጨረሱም የወደቀው አገልጋይ ‹‹ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ›› የሚል ፈጣን ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ በግል ሕይወትም ኾነ በጓደኛችን ሕይወት ዙርያ ሱባዔ ስንገባ እግዚአብሔር ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

፪. ከቅዱሳን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶች እና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ‹‹ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ፤›› (ኢሳ. ፶፮፥፮) በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት ከበረከታቸው መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት ከጥንት ጀምሮ የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡

ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የልዩ ልዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል (ለመሳተፍ) የቅዱሳን ዐፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ፪፥፱ ላይ እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በኤልሳዕ ላይ እጥፍ ኾኖ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት (ዅሉንም ነገር በመተው) የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ ሰዎች መኖራቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ይቆየን

ይቀጥላል

የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ቅበላ የኅሊና ዝግጅት ወይስ?

ይህንን ጽሑፍ በ2007ዓ.ም በwww.eotcmk.org ለንባብ ያበቃሁት ሲሆን ዛሬም ሰሞነኛ ሆኖ መጥቷልና መልካም ንባብ።

ቅበላ ማለት የጾም ዋዜማ ፣ጾም ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ ያለው ቀን ወይም ሰሞን ማለት ነው፡፡ በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት ሰንበታት፣ አጽዋማትና በዓላት በዋዜማው በጸሎት (በምኅላ)፣በመዝሙር፣በትምህርት ወዘተ. ልዩ አቀባበል ይደረግላቸዋል ፡፡

ለምሳሌ አይሁድ ሰንበትን(ቅዳሜ) ሲያከብሩ በዋዜማው አቀባበል ያደርጉላታል፡፡

ዓርብ ፀሐይ ሲገባ ካህኑ ደውል ይደውላሉ አሊያም በቤት ያለ የቤቱ አባወራ የሰንበት መግቢያ ሰዓት መቃረቡን ድምጽ በማሰማት ያሳውቃል፡፡ በአካባቢው ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡ በአንድ ላይ ሆነው ወደ ፀሐይ መውጫ ይሰግዳሉ፡፡ ጸሎት ይደረጋል፡፡ ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል፣አሥርቱ ቃላት ሌሎችም ንባባት ይደገማሉ፡፡ ማብራት ተይዞ “ዕለተ ሰንበት እንኳን ደህና መጣሽ” ብለው ያከብሯታል፡፡ ከሦስት ሰዓት በኋላ እራት ይበላሉ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡

አይሁድ(በሀገራችን ቤተ እስራኤላዊያንም) የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው በፊት የሰባት ቀን ጾም ይጾማሉ፡፡ በዋዜማው(ቅበላ) ይሆናል፡፡ በኦሪት ዘጸአት12፡5 ከግብጽ ባርነት ነጻ ስለመውጣታቸው እንደተጠቀሰው ለፋሲካ ጾም አቀባበል ያደርጋሉ፡፡ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ወስደው በወሩ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቀው የእስራኤል ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ያርዱታል፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት መቃኑና ጉበኑን ይቀቡታል።በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይበላሉ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።ጥሬውንና በውኃም የበሰለውን አይበሉም፡፡ … የቀረ ቢኖር በእሳት ያቃጥላሉ ፡፡ያልቦካ ቂጣ ይበላሉ፡፡

ይህንን አድርገው መጻሕፍት ያነባሉ፣ጸሎት ያደረጋሉ፡፡ በጾማቸው ወቅት ተጠንቅቀው ጾመው ይጨርሱና የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡

ይህ ሁሉ ለሀዲስ ኪዳን ምሳሌ ነበር፡፡ጾሙን የመሠረተልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የፋሲካው በግም እርሱ ነው፡፡ነጻ ያወጣንም ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነው፡፡

ቅበላ በተለይ የነነዌ ጾም እንዳለቀ ዐቢይ ጾም /ጾመ ሁዳዴ መስከረም አንድ ቀን በታወጀው መሠረት ቀናት ሲቀረው መናንያን፣ ካህናትና ምእመናን ጾሙን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች ያደረጋሉ፡፡ ጾሙ አባ ዲዮስቆሮስ ስለ ዐቢይ ጾም ታላቅነት “ከመ እንተ ብእሲ ለጸዊም በውስተ ገዳም ኃደረ። እምኀበ ዲያብሎስ ተመከረ በኃይለ መለኮቱ መኳንንተ ጽልመት ሠዓረ፤ እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም ፵ መዓልት ፵ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ኖረ። ከዲያብሎስ ዘንድ በሦስት አርእስተ ኃጣውዕ ተፈተነ፥ ድል ይነሣልን ዘንድ። ፭ ሺህ ከ፭ መቶ ዘመን ሰልጥነው የኖሩትንና የጨለማ ገዥ የሆኑትን ሠራዊተ ዲያብሎስን በጌትነቱ ሻረልን።” እንዳለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድረገን በመጾም በዚህ ዓለም ስንኖር ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስን ድል ለማድረግ፣በጾሙ በረከት፣ ጸጋና መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት እንድንበቃ የምናደርገው የዝግጅት ሰሞን ነው፡፡

በቅበላ ሰሞን አባቶቻችን በየገዳማቱና አድባራቱ ለቤተ እግዚአብሔር መገልገያ የሚሆኑ ንዋያትንና መብዓ ያዘጋጃሉ፡፡ስምንቱን የዐቢይ ጾም የሱባዔ ሳምንታት የሚያሳልፉበትን ቦታ ይመርጣሉ፡፡ ለጸሎት የሚያግዟቸውን መጻሕፍት ያዘጋጃሉ፡፡

በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት ለማሳለፍ ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ ጥሉላት(የእንስሳትና የዓሣ ሥጋ፣የእንስሳት ውጤቶች) ምግቦችን ካስፈለጋቸው ለህሊናቸው ዕረፍት ለመስጠት በመጠኑ ይመገባሉ ጾመው ለማበርከትና ዋጋ ለማግኘት፡፡ በከተማና በገጠር የሚገኙ ምእመናንም ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ፣አልባሳት ሲገዙ ይሰነብታሉ፡፡ አልፎ አልፎም ጾሙን በንጹህ ህሊና ለመጀመር ከአበ ነብሳቸው ጋር ይወያያሉ፡፡ “ወኢትፍራሕ ተጋንዮ በእንተ ኃጢአተከ ኃጢአትህን ለማመን ለመናገር አትፍራ፡፡” እንዳለ ሲራክ 3፡18፡፡ የበደሉ ማሩኝታ የተጣሉም ይቅርታ ይጠይቃሉ ፡፡ ነግቶ ለኪዳን፣ ቀኑን ለቅዳሴና ለሠርክ ጸሎት ለማወል ያቅዳሉ፡፡ መዝሙር ቤቶችም የበገናና ዘለሰኛ መዝሙራትን ያሰማሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ቅበላ ሲባል በአብዛኛው አዕምሮ የሚከሰተው ከሰባው አርዶና አወራርዶ አሊያም ልኳንዳ ቤት ተሰልፎና ታድሞ፣ጥሉላት ምግቦችን በዓይነት አሰልፎ፣ ጠጅ (አልኮል) ተጎንጭቶ፣ከመጠን ያለፈ ደስታ ፈጥሮ ጾሙን መቀበል ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ 1ኛጴጥ 5፡8 “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” እንዳለው ከመጠን ያለፈ ማንኛውም ደርጊት ለፈተና ብሎም በዲያቢሎስ ሊያስማርከን ይችላል፡፡

አንድ መምህር ሲያስተምር የሰማሁት ሴትየዋ በቅበላ ብዙ የጥሉላት ምግቦችን አዘጋጅታ ስትመገብ ሰንብታ ጾሙ ሲገባ ምግቡ ሳያልቅ ይቀራል፡፡ አላስችል ብሏት በጾሙ የመጀመረያ ሳምንት የተረፈውን ምግብ ትመገባለች፡፡

ይህችን እናት የህሊና ወቀሳ እረፍት ነሳት ለአበ ነብሷ(ለንስሀ አባቷ) መንገር ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተረድታ ያደረገችውን ነገረቻቸው፡፡ አበ ነብሷም አስተምረው ቀሪውን ጾም በተገቢው ሁኔታ እንድትጾም መክረው ይሸኟታል፡፡ ጾሙ ሊያልቅ ሲቃረብ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ 1ቆሮ 15፡33 ከማይጾሙ ጓደኞቿ ጋር በመዋሏ የጥሉላት ምግብ ትመገባለች፡፡ አሁንም ከህሊና ወቀሳ መዳን ስላልቻለች ለአበ ነብሷ ለመናገር ወስና ነገረቻቸው፡፡አበ ነብሷም የሴትየዋን ስም ጠርተው “ምነው! ጾሙ ሲገባ አላስገባ አሁን ሊወጣ ሲል አላስወጣ አልሽ ፡፡ ”አሏት ይባላል፡፡

ጾም አቀባበል የሚደረግለት መንፈሳዊነትን ባለቀቀ መልኩ በመጠኑ ሲሆን፤በመጾማችን ድል የምናደርግበት፣በመንፈስ የምናድግበት፣የቤተክርስቲያን ልጅነታችንን የምናረጋግጥበት(ቀኖናና ሥርዓቷን ስለምንጠብቅ) ይሆናል፡፡

ስለዚህ ዝግጅታችን ምን ይሁን?

ጾሙን ተቀብለን፤ ጾመን፣ጸልየን፣መጽውተን ሰግደን ዋጋ እንድናገኝ እግዚአብሔር ይርዳን።

ጥር 26ቀን 2010ዓ.ም

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

††† እንኳን ለቃና ዘገሊላ እና ለቅዱሳን ያዕቆብ ወቴዎድሮስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

<<< ቃና ዘገሊላ >>>

††† "ቃና" የሚለው ቃል በሃገራችን ልሳን (በአማርኛ) የምግብን: የመጠጥን ጥፍጥና ወይም በጐ መዓዛን የሚያመለክት ነው፡፡ ምን-አልባትም ከዚህ በዓል ምሥጢር የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን ቃና ከገሊላ አውራጃዎች አንዷ ናት። ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚህች ሥፍራ ተገኝቶ በድንግል እናቱ ምልጃ ታላቅ ተአምርን በዚህች ዕለት ሠርቷል። "ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው (Miracle) የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ): ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል።

ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ / ከሐሌ ኩሉ / ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው። እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ (1ነገሥትን ተመልከት) እንደ ነበር ይታወቃል። እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:8, 17:20, ማር. 16:17, ሉቃ. 10:17, ዮሐ. 14:12) እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። (ሐዋ. 3:6, 5:1, 5:12, 8:6, 9:33-43, 14:8, 19:11) ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ በወንጌሉ ምዕራፍ 2 ላይ እንዳስቀመጠው የቃና ዘገሊላው ተአምር የመጀመሪያው ነው። "ወዝንቱ ቀዳሜ ተአምር . . ." እንዲል። (ዮሐ. 2:11) ያ ማለት ግን ጌታ ከዚያ በፊት ተአምራትን አልሠራም ማለት አይደለም።

ይልቁኑ ራሱን ከገለጠና ከተጠመቀ በሁዋላ የሠራው የመጀመሪያው ተአምር ነው ሲል ነው እንጂ። ምክንያቱም መድኃኒታችን እንደ ተጠመቀ ዕለቱኑ ገዳመ ቆረንቶስ ገብቷልና። (ማቴ. 4:1) አንድም በቃና ሌሎች ተአምራትን የሚሠራ ነውና ይህ ተአምር በቃና የመጀመሪያው ሆነ።

ትክክለኛው የቃና ዘገሊላ ቀን የካቲት 23 ነው። ጥር 11 ተጠምቆ: የካቲት 21 ቀን ከጾም ተመልሷል። ከዚያም የካቲት 23 ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ሒዷል። ነገር ግን አበው መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው የውሃ በዓል ከውሃ በዓል ጋር ይስማማል ብለው ጥር 12 አድርገውታል።

በቃና ዘገሊላ ሙሽራው ዶኪማስ ሲሆን ባለ ሠርጉ ደግሞ አባቱ ዮአኪን ነው። ይህም ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል አጐቱ ነው። የልጁ ጋብቻ የተቀደሰ ይሆን ዘንድም ጌታ ክርስቶስን: ድንግል እናቱንና ባለሟሎቹ ሐዋርያትን ወደ ሠርጉ ጠራ።

ምንም እንኩዋ መድኃኒታችንና እመቤታችን ከድግሱ የማይበሉ ቢሆኑም (በትሕርምት ኗሪዎች ነበሩና) ጠሪውን ደስ ለማሰኘት ሠርጉን: ለመቀደስና የጋብቻን ክቡርነት ለማሳየት አብረው ታደሙ። የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ሲጀመር በድንኩዋኑ ውስጥ ጌታ ከመካከል ተቀመጠ። ድንግል በቀኙ: ዮሐንስ በግራው ሲቀመጡ: ሌሎች ሐዋርያት ግራና ቀኝ ከበው ተቀመጡ። ሲበላና ሲጠጣ ድንገት የተደገሰው ምግብና መጠጥ አለቀ። ደጋሾቹ በጭንቅ ላይ ሳሉም አይጠና ሆዷ ድንግል እመ ብርሃን የሆነውን አወቀች። እንዴት አወቀች ቢሉ:- በጸጋ: አንድም "ከልጅሽ አማልጂን" ብለው ቢለምኗት ነው ይሏል። እመቤታችን በዚያ ጊዜ ወደ ልጇ ቀርባ ቸር ልጇን "ወይንኬ አልቦሙ-ወይኑኮ አልቆባቸዋል" አለችው።

ለጊዜው ወይኑም: ምግቡም ስላለቀባቸው እንዲህ አለች። በምሥጢሩ ግን ወይን ያለችው ፍቅርን: ቅዱስ ቃሉንና ክቡር ደሙን ነው። ጌታም ይመልሳል:- "ምንት ብየ ምስሌኪ ኦ ብእሲቶ: ዓዲ ኢበጽሐ ጊዜየ-አንቺ ሆይ! (እናቴ ሆይ!) ያልሺኚን አላደርግ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ? ነገር ግን ጊዜው ገና አልደረሰም ብየ ነው እንጂ" አላት። ምክንያቱም ጌታ:-

 • የወይን ጋኖቹ እስኪያልቁ ይጠብቅ ነበር። (አበረከተ ይሉታልና)
 • አንድም ይሁዳ ወጥቶ ነበርና እርሱ እስኪመለስ ነው። (እኔ ስወጣ ጠብቆ ተአምር ሠራ ብሎ ለክፋቱ ምክንያት እንዳያቀርብ)

አንድም "ወይን (ቅዱስ ደሜን) የምሰጠው በቀራንዮ አንባ ነው" ሲል "ጊዜየ ገና ነው" ብሏታል። አንዳንድ ልቡናቸው የጠፋ ወገኖቻችን ጌታ እመቤታችንን እንዳቃለላት (ሎቱ ስብሐት! ወላቲ ስብሐት!) አስመስለው ይናገራሉ። ይህንን እንኩዋን ጌታ ባለጌዎቹ እነሱም አያደርጉት። "አባትህንና እናትህን አክብር" (ዘጸ. 20) ያለ ጌታ እንዴት ለእናቱ ክብርን ይነፍጋል? ልቡና ይስጠን! ወደ ጉዳያችን ስንመለስ መድኃኒታችን እንዲህ ሲል መለስላት። ተግባብተዋልና እመ ብርሃን አሳላፊዎቹን "ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ-የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ" አለቻቸው። (ዮሐ. 2:5) ጌታም በ6ቱ ጋኖች ውሃ አስሞልቶ በተአምራት ወይን አደረጋቸው። እንጀራውን ወጡን በየሥፍራው ሞላው። ታላቅ ደስታም ሆነ። የአሳላፊዎቹ አለቃም (ለአባታችን አብርሃም ምሳሌ ነው) ከወይኑ ጥፍጥና የተነሳ አደነቀ። በዚህም የድንግል ማርያም አማላጅነት: የመድኃኒታችን ከሃሊነት ታወቀ: ተገለጠ።

††† ቅዱስ ያዕቆብ ርዕሰ አበው †††

የአባቶች አለቃ የተሰኘ ቅዱስ ያዕቆብ ለ2ቱ ታላላቅ አባቶቹ እርሱ 3ተኛቸው ነው። እነርሱን መስሎ: እነርሱንም አህሎ በጐዳናቸው ተጉዟል። በፈቃደ እግዚአብሔር ብኩርናን ከኤሳው ተቀብሎ ወደ ሶርያ ሲሸሽ ቤቴል (ፍኖተ ሎዛ) ላይ ድንጋይ ተንተርሶ በተኛበት ግሩም ራዕይን አይቷል። ይህችውም የወርቅ መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። "አንቲ ውዕቱ ሰዋስው ዘርእየ ያዕቆብ" እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ) ተነስቶም "ዛቲ ይእቲ ኈኅታ ለሰማይ: ዝየ ይትሐነጽ ቤተ እግዚአብሔር - ይህች የሰማይ ደጅ ናት: ቤተ እግዚአብሔርም ይታነጽባታል" ብሎ ትንቢት ተናግሯል።

ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል። ከ2ቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) : ከ2ቱ ደንገጥሮች 12 ልጆችን ወልዷል። ከአጐቱ ከላባ ዘንድ ለ21 ዓመታት አገልግሎ: ሃብት ንብረቱን ጠቅልሎ ወደ ርስቱ ከነዓን ሲመለስ ለብቻው ራቅ ብሎ ይጸልይ ገባ። በዚያም እግዚአብሔር ሲታገለው አደረ። (ይኸውም የፍቅርና የምሥጢር ነው) ለጊዜው ጌታ ያዕቆብን "ልቀቀኝ" ቢለው "ካልባረከኝ አለቅህም" አለው። ጌታም ስሙን "እሥራኤል" ብሎ ባርኮታል። ቅዱስ ያዕቆብ በስተእርጅና ብዙ መከራ አግኝቶታል። ልጁን ዮሴፍን ወንድሞቹ ሽጠው "አውሬ በላው" ብለውታልና በለቅሶ ዐይኑ ጠፋ። በረሃብ ምክንያትም በ130 ዓመቱ ከ75 ያህል ቤተሰቦቹ ጋር ወደ ግብጽ ወረደ። በዚያም ለ7 ዓመታት ኑሮ በ137 ዓመቱ ዐርፏል። ልጆቹም ቀብረውታል።

††† ኃያል ቴዎድሮስ በናድሌዎስ †††

 • በ3ኛው መቶ ክ/ዘ በምሥራቅ (በአንጾኪያ) ያበራ:
 • ድንግልናውን በንጹሕ የጠበቀ:
 • ቅዱሳን መላእክት የሚያነጋግሩት:
 • የአንጾኪያ ሠራዊት ሁሉ አለቃ የነበረ:
 • በጦርነት ተሸንፎ የማያውቅ።
 • አሕዛብ ስሙን ሲሰሙ የሚንቀጠቀጡለት:
 • ከአማልክት ወገን ነው እያሉ የሚፈሩት:
 • እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ የሚያመልክ የወቅቱ ወጣት ክርስቲያን ነው።

ዲዮቅልጢያኖስ በካደ ጊዜም ከባልንጀሮቹ ለውንድዮስና ኒቆሮስ ጋር መላእክት ወደ ሰማይ አሳርገውታል። በዚያም መድኃኒታችን ክርስቶስን ፊት ለፊት አይቶ: በእሳት ባሕርም ተጠምቁዋል። በዚህች ቀንም ከቅዱሳን ለውንድዮስና ኒቆሮስ: እንዲሁ ከ2.5 ሚሊየን ሰራዊቱ ጋር ለመከራ ተሰጥቷል። እርሱንም በ153 ችንካር ወግተው ገድለውታል።

††† አምላከ ቅዱሳን ወይነ ቃና ፍቅሩን ያሳድርብን። ከድንግል እናቱ ምልጃና ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን።

††† ጥር 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

 1. ቃና ዘገሊላ
 2. ቅዱስ ያዕቆብ እሥራኤል
 3. ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ
 4. ቅዱሳን ለውንድዮስ እና ኒቆሮስ
 5. "2.5 ሚሊየን" ሰማዕታት (የቅዱስ ቴዎድሮስ ማሕበር)

††† "አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ። ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም። ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ:- 'ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል። ከሰከሩም በሁዋላ መናኛውን። አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል' አለው።" (ዮሐ. 2:9)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከዲ/ን ዮርዳኖስ ማስታወሻ

††† እንኳን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጥምቀት በዓል (ኤጲፋንያ) በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

<<< በዓለ ኤጲፋንያ >>>

††† "ኤጲፋንያ" የሚለው ቃል ከግሪክ (ጽርዕ) ልሳን የተወሰደ ሲሆን በቁሙ "አስተርእዮ: መገለጥ" ተብሎ ይተረጐማል። በነገረ ድኅነት ምሥጢር ግን ኤጲፋንያ ማለት "የማይታይ መለኮት የታየበት: እሳተ መለኮት በተዋሐደው ሥጋ የተገለጠበት" እንደ ማለት ነው።

"ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ። እሳት በላዒ አምላክነ።" እንዲል። (አርኬ)

አንድም: ምሥጢር ሆኖ የቆየ አንድነቱ: ሦስትነቱ የተገለጠበት ቀን ነውና ዕለተ ጥምቀቱ ኤጲፋንያ ይሰኛል። መድኃኒታችን ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ያድን ዘንድ ከሰማያት ዙፋኑ ወርዶ: እንደ ሰውነቱ በሥጋ ማርያም ለ33 ዓመታት ተመላልሷል። ጊዜው ሲደርስም በፈለገ ዮርዳኖስ: ከዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ ሔደ። መድኃኒታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደው ጥር 10 ቀን አመሻሽ ላይ ሲሆን በፍጹም ትሕትና ተራ ሲጠብቅ አድሮ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ደረሰውና ሊጠመቅ ቀረበ። አሥር ሰዓት መሆኑም ርግብ (መንፈስ ቅዱስ) ሲወርድ ሰዎች ሥጋዊት ርግብ ናት ብለው እንዳይጠራጠሩ ነው። ርግብ በሌሊት መንቀሳቀስ አትችልምና። መድኃኒታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠጋ አምላክነቱን ተረድቶ "እንዴት ፈጣሪየ ወደ እኔ ትመጣለህ? እንዴትስ በእኔ እጅ ትጠመቃለህ?" አለው። ትህትና ለእናትና ልጅ ልማዳቸው ነውና። ጌታ ግን "ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል" ሲል እንዲያጠምቀው ፈቀደለት። ቅዱስ ዮሐንስም "ስመ አብ በአንተ ሕልው ነው። ስመ ወልድ ያንተ ነው። ስመ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ዘንድ ሕልው ነው። በማን ስም አጠምቅሃለሁ?" ሲል ጠየቀው። ጌታ "ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሐለነ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ" እያልክ አጥምቀኝ አለው። ትርጉሙም "የቡሩክ አብ የባሕርይ ልጁ : ብርሃንን የምትገልጥ ሆይ ይቅር በለን! አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዓለም ካህኑ ነህና" እንደ ማለት ነው። ከዚያም ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ባሕር አይታ ደነገጠች : ሸሸችም። (መዝ. 76:16, 113:3) ዮርዳኖስ ጨንቆት ግራ ቀኝ ተመላለሰ። እሳተ መለኮት ቆሞበታልና ውኃው ፈላ። በጌታ ትዕዛዝ ግን ጸና። ጌታ ተጠምቆ: ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶ: ዮርዳኖስን ብርህት ማሕጸን አድርጐ: የእዳ ደብዳቤአችንንም ቀዶ ከወጣ በኋላ ሰማያት ተከፈቱ። ማለትም አዲስ ምሥጢር ተገለጠ። አብ በደመና ሆኖ "የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኜ ልመለክበት የመረጥኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው!" ሲል በአካላዊ ቃሉ ፍጹም ተዋሕዶን መሰከረ። መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ። ራሱንም ቆንጠጥ አድርጐ ያዘው። በዚህም የሥላሴ አንድነቱ: ሦስትነቱ ታወቀ: ተገለጠ። ቅዱስ ዮሐንስ "መጥምቀ መለኮት" የሚባልበትን ታላቁን ክብር ሲያገኝ ዮርዳኖስ የልጅነት መገኛ ቅዱስ ባሕር ሆነ።

<<< ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ >>>

ቅዱስ ወንጌል ላይ ቅዱስ ሉቃስ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል። (ሉቃ. 1:6) እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልዓከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች። በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው። የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል" አሉ። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት። ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት። ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።

ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው። "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና። (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና። ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና። ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ: ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ። የሚገባበትም ጠፋው። "እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው። ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው። ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል። (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

=>"አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ /የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች"

 1. ነቢይ
 2. ሐዋርያ
 3. ሰማዕት
 4. ጻድቅ
 5. ካሕን
 6. ባሕታዊ / ገዳማዊ
 7. መጥምቀ መለኮት
 8. ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
 9. ድንግል
 10. ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
 11. ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
 12. መምሕር ወመገሥጽ
 13. ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>አምላከ ቅዱሳን በጥምቀቱ ይቀድሰን። ከበረከተ ጥምቀቱም ያድለን።

=>ጥር 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት

 1. በዓለ ኤጲፋንያ
 2. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
 3. አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
 4. አባ ወቅሪስ ገዳማዊ
 5. አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት
 6. ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት

 1. ቅዱስ ያሬድ ካህን
 2. ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
 3. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
 4. ቅድስት ሐና ቡርክት

=>"ጌታ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ። እነሆም ሰማያት ተከፈቱ። የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ: በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ። እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ:- 'በእርሱ ደስ የሚለኝ: የምወደው ልጄ ይህ ነው' አለ።" (ማቴ. ፫፥፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከዲ/ን ዮርዳኖስ ማስታወሻ

የጥምቀት ከተራ በዓል አከባበር የተመጣ

በየዓመቱ የጥምቀት በዓል በድመቀት ይከበራል፡፡ ከበዓሉ በፊት የከተራ በዓል የሚከበርበትን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ፋይዳው ምንጩ ምንድን ነው፡፡

ይህን ጽሑፍ ጥር 9 ቀን 2006 ዓ.ም በማኅበረቅዱሳን ድረ-ገጽ/ www.eotcmk.org አውጥቼው የነበረ ሲሆን አሁን መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል፡፡

ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡

“ከተራ” በመባል የሚታወቀው – ዋዜማው” ሠርግው /1981፣8/ እንደገለጹት “ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ከተራ ፍቺውም ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡” ብለው ሲፈቱ፣ ደስታ ተከለ ወልድ /1962፣ 694/ ደግሞ የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር 10 የጠራ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት ታቦትና ሰው ወደ ዠማ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት ይፈቱታል፡፡

ኪዳነ ወልድ ክፍሌም /1948፣ 555/ ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣ “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው፡፡

የቀደሙ አባቶቻችን በተለይ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡

በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡

የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡ ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ(1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡

ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።/ሐመር ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም/ ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ዘፀ 25÷1 እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤ ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡

ሊቃውንቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድራሉ። የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ የዋዜማው ቀለም ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡

በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘’ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡ የበዓሉን ሂደት ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ሲነሳ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ›› ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦቱ ወጥቶ ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ ይዘመራል፣ ይጸነጸላል፣ ይመላለሳል፡፡

የወርቅ ካባና ላንቃ የለበሱ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡ የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦቱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ትርዒት እያሳዩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም የአማርኛ መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎችም ምስጋናዎችም እየቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡ የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ ተደግሞ ታቦታ ሕጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ /ሠርግው፤ 1981፣ 9/፡፡

በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል ካህናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9፡00 ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በነጋታው የሥርዐተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡ የከተራ በዓል ምሳሌያት በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡

የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም/ይከተር/ ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል /ኢያሱ 3÷8-9/፡፡

ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት ካህናት ከወንዙ መሀል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት›› ይህም ‹‹የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው›› በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡

ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ታቦቱ የጌታችን፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ፡፡›› /ኪ.ወ.ክ ፤517/፡፡

ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን ‹‹ማይ ሹም›› በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ” በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን /ጃንሜዳን/ ወዘተ ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ፡፡እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡

በጥምቀት ከእግዚአብሔር ያገኘነውን ልጅነት ጠብቀን እንድኖር አምላካችን ይርዳን

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ጥር 8ቀን 2010ዓ.ም

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን ያገለገለ፤ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፤ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፤ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡

ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹… ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ … ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብምበጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ሲል ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ፣ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዅሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡

ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅ እና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡

ካህኑ ዘካርያስም መልአኩን ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራችእንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡

ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በኹኔታውም በቤተ መቅደስ ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ሆኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ›› ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ዘመነ ብሉይ ሊፈጸም፣ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን (በሥጋ ሊገለጥ) ስድስት ወራት ሲቀረው፣ ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ዘመዶቹ ስሙን በአባቱ መጠርያ ‹ዘካርያስ› ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን ‹‹ዮሐንስ ይባል›› አለች፡፡

የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ ‹ዮሐንስ› ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም ‹‹… አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡

የኀጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉትያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ነቢይነት እና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት አብሣሪነት የሚመለከት ትንቢት አስቀድሞ ተናገሯል (ሉቃ. ፩፥፶፯-፸፱)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ (ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ )

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ገድልና ዕረፍቱ ይቀጥላል

ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ 30ቀን፤ የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ. 1:1-8

የሐሙስ ጉባኤ ትምህርቶች

በዓለ ጰራቅሊጦስ ግንቦት ፲፱/፳፻፲ ዓ.ም.

"በዓለ ስምዖን" መምህር ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና

የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ ወረቦች

መስከረም ፳፻፲ ዓ.ም. ዋዜማ

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መስከረም ፳፻፲ ዓ.ም. ዋዜማ ያስተማሩት የባህረ ሃሳብ ትምህርት።

መስከረም ፳፻፲ የቅዳሴ ስረዓት


በዓለ ንግሥ

ወርሃ መስከረም የቅዱስ ዮሐንስ በዓል የሚከበርበት ነው፡፡ መስከረም ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቃልኪዳን የተቀበለበት፣ ሄሮድስ አንገቱን የቆረጠበት ጌታም በተአምር ለቅዱስ ዮሐንስ አንገት ክንፍ ሰጥቶ ተጨማሪ አሥራ አምስት አመት እንዲያስተምር ሕይወት የሰጠበት፣አባቱ ቅዱስ ዘካርያስም በቤተ መቅደስ ደጃፍ በሄሮድስ ወታደሮች የተሰዋበት እና እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥም በበርሃ ያረፈችበት ወርሃ መስከረም ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተሰየመው ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በአሜሪካ፣ በሜሪላንድ ግዛት በሞንትጎሞሪ አካባቢ ነዋሪ ለሆኑ የተተከለ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህም ቤተክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በታላቅ ድምቀት መስከረም ፲፬ ፳፻፲ (September 24, 2017) ተከብሮ ውሏል። በዚህም ዕለት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በስሜን አሜሪካ በድሲ አና ካሊፎርንያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናት፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ተገኝተዋል። በበዓሉ መገኘት ላልቻላችሁት፣ ከበረከቱ አንድትካፈሉ አነዚህን ምስል ወድምጽ ተጋብዛችኋል፡፡

ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት :- ነቢየ ልዑል፣ ሰማዕት፣ ካህን፣ ወሐዋርያ - መምህር ብርሀኑ አድማስ


ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: ዓርኩ ለመርዓዊ ትሰመይ: ወአዝማዱ በሥጋ ትሰመይ: ተፈኖከ ታርኁ አናቅጸ ጽድቅ

መስከረም ፳፻፲ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በዓለ ንግሥ

ማስታወቂያ

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በስሜን አሜሪካ በድሲ አና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል

መልዓከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ የደብሩ አስተዳዳሪ

መልዓከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ

አኛን ለማግኝት

ስልክ: (585)261-9494, (240)750-7487

ኢሜይል: info@hbkyohannes.org

ድረ ገፅ: www.hbkyohannes.org

አድራሻ:


7401 Muncaster Mill Rd
Gaithersburg, MD 20877

ቋሚ ፕሮግራም

ቅዳሴ

ዘዎትር አሁድ ከ6am ጀምሮ

የሰንበት ት/ቤ

ዘዎትር አሁድ ከ8am ጀምሮ

ጉባኤ አና ትምህርት

ዘዎትር ሀሙስ ከ6pm ጀምሮ